tgoop.com/behlateabew/7559
Last Update:
ደክሜ ባለሁ ጊዜ ከወደቅሁበትም መነሳት ሲከብደኝ ለነፍሳት ርኅሩኅ የሆንሽ ድንግል ሆይ ወደእኔ ነይ። ታማሚው ልጅሽ ከደጅሽ ቆሜ አለሁ፤ ሕመሜን ግን አንቺ ከእኔ በላይ ታውቂዋለሽ፥ ባለመድኅኒቱም ልጅሽ ነው።
ድንግል ሆይ "ልትድን ትወዳለህን?" እባክሽ አትበይኝ። መታመሜን የማላውቅ ጎስቋላ በሽታዬን የምመርጥ ሞኝ ነኝና። በሲቃ ነፍሴ ወደአንቺ ትጣራለች፥ ወደልጇ ይዘሻት እንድትወጪ ዐይን ዐይንሽን ታይሻለች።
ንጹሕ ለሆንሽ ለአንቺ የማቀርበው የሚመጥን እጅ መንሻ ከእኔ ዘንድ የለኝም፥ ለአዳም ዘር ስጦታ ሆነሽ በእግዚአብሔር ለተሰጠሽ ለአንቺ ከቶ ምን ማቅረብ እችላለሁ? ስለዚህም ድንግል ሆይ እንደምታስፈልጊኝ አውቀሽ ሕይወትን ለሚሞላ ልጅሽ "ብርታት አልቆበታልና ና ወደእርሱ ዘንድ እንሂድ" በይው፣ የቸሩ እረኛ ደግ እናት ሆይ ተኩላዎች ከልጅሽ በጎች እንዳይለዩኝ ወደእኔ ነይ፣ በመንገድ ወድቄ እንዳልቀር የደጉ ሳምራዊ እናት ሆይ ባለመድኅኒት ልጅሽን ይዘሽ ወደእኔ ነይ፣ ጉድፍ የሌለብሽ መሶበወርቅ ሆይ ተርቤያለሁና የሕይወት ሕብስት ልጅሽን ታቅፈሽ የነፍሴን ረሀብ ታስታግሺልኝ ዘንድ ነይ፣ የምግባር እንስራዬ ባዶ ነውና ከምንጭ ዳር እጠብቅሻለሁ ጥምን የሚያጠፋ የሕይወት ውሃ ልጅሽን ይዘሽ ነይ፣ መንገድ ጠፍቶኝ እጠብቅሻለሁ መንገድ እና ሕይወት እውነትም የሆነውን ልጅሽን ይዘሽ ወደእኔ ነይ፥ ብርታት አጥቻለሁና እኔ እስክመጣ አትጠብቂኝ ሰላማዊቷ ርግብ ሆይ አንቺ ቀድመሽ ወደእኔ ነይ።
@ዲያቆን እስጢፋኖስ ግርማ
BY ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

Share with your friend now:
tgoop.com/behlateabew/7559