tgoop.com/butajira_Qirat_daewa_group/1482
Last Update:
ረመዷን እና ተውበት
እንደሚታወቀው ታላቁ የረመዷን ወር ሊገባ የተወሰኑ ቀናት ብቻ ቀርተውታል።እናም መቃረቡን አስመልክቶ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህንን ወር ካጠፋናቸው ጥፋቶች ወደ አሏህ በፀፀት ተመልሰን በንፁህ ልብ መቀበል እንዳለብን በሰፊው ትምህቶች ሲሰጡ ይስተዋላል።ይሁን እንጂ እነዚህን ትምህርቶች በቅጡ ያልተረዱ ወንድሞችና እህቶች ስህተቶችን ሲፈፅሙ ይታያል።ከነዚህ ስህተቶች መካከል አንዱን ብቻ ለማሳያነት ልጥቀስ
\\ ረመዷን ሲመጣ ሁሉም በሚባል ያህል ሙስሊሙ ኡማ ባለቺው እውቀት ልክ ይዘጋጃል።ከነዚህ ዝግጅቶች መካከል በተውበት ወደ አሏህ መመለስ አንደኛውና ዋንኛው ነው።ነገር ግን ተውበታችን ተውበታችንን በሚያበላሽ እሳቤ( ኒያ) ላይ ተመስርቶ ይታያል።ይህ እሳቤ ምንድነው ካላቹህ ? መልካም !! ነገሩ ወዲህ ነው, ገና ተውበት ስናደርግ ለተውበታችን የመነሻና የመድረሻ ጊዜ ገደብ እናበጅለታለን።
ለምሳሌ፦ አንድ ሶላት የማይሰግድ ሰው ረመዷንን ከዚህ ጥፋቱ ተመልሶ መቀበል ይፈልጋል።ነገር ግን ሶላቱን የሚጀምረው የረመዷን የመጀመሪያው ቀን ወይም ከሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ይሆናል፤ይህም ብቻ አይደለም ረመዷን መጨረሻ አካባቢም በነሻጣ የጀመረውን ሶላት አቋርጦ ፆሙን ብቻ ያስቀጥላል። የዚህን ሰው ተውበት ስናይ የተውበትን መስፈርት ያሟላ አይደለም።ምክንያቱም ተቀባይነት ያለው ተውበት በጥቂቱ ሶስት መስፈርቶችን ያሟላ መሆን አለበት።እነርሱም
➊ ተውበት ለማድረግ ከወሰነበት ሰዓት ጀምሮ ከወንጀሉ ተነቅሎ መውጣት
➋ በሰራው ወንጀል መፀፀት
➌ ዳግም ወደዛ ወንጀል ላለመመለስ ቁር፞ጥ ያለ ውሳኔ መወሰን
★ ከላይ ለምሳሌነት ያነሳነው ሰውዬ ግልፅ በሆነ መልኩ የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን መስፈርት ያሟላ አይደለም።ምክንያቱም ተውበት ለማድረግ የወሰነው ምናልባት ረመዷን ሳምንት ሲቀረው ይሆናል ነገር ግን ሶላቱን የሚጀምረው ረመዷን ሲገባ ነው።ይህም ማለት ተውበት ለማድረግ ከወሰነበት ሰዓት ጀምሮ ከወንጀሉ ( ሶላቱን ከመተው) አልወጣም ማለት ነው።በዚህ መሰረት የመጀመሪያውን መስፈርት አጓድሏል።ሌላኛው ደሞ ረመዷን ሲወጣ አብሮ ሶላቱንም ይተዋል።ይህ ከሆነ ደሞ ተውበት ስናደርግ ዳግም ወደዛ ጥፋት ላለመመለስ ቁር፞ጥ ያለ ውሳኔ መወሰን አለበት ብለን ሶስተኛ ላይ ያሰቀመጥነውን መስፈርት ያላሟላ ሆኖ ይገኛል ማለት ነው።ተውበታችን ደሞ ተቀባይነት የሚኖረው ሁሉንም መስፈርት ስናሟላ ነው።ያለበለዚያ ተውበታችን አሁን አፏን ጠርጋ ምንም ሳትቆይ ዳግም ቆሻሻ ለመልቀም እንደመትመለሰው ዶሮ ነውና የሚሆነው ልንጠነቀቅ ይገባል።ሶላቱን ካሁኗ ሰዓት ጀምረን ላለማቋረጥ ወስነን መጀመር አለብን። ለምሳሌ ብለን ሶላትን መተው አነሳን እንጂ ከሌሎችም ጥፋቶቻችን ስንመለስ በዚህ መልኩ መሆን ይኖርበታል።
እናስተዉል!!
ተውበት ማለት ካሳለፍናቸው የወንጀል ቆሻሾቻችን የምንፀዳበት የአዛኙ ጌታችን ትልቅ ስጦታ መሆኑን ማስተዋል ይጠበቅብናል።ተውበት ማድረግ ባይኖር እና በእያንዳንዱ ወንጀላችን አሏህ ቢተሳሰበን ምን ይውጠን ነበር!? የትስ እናመልጥ ነበር? ስለዚህ ወንድም እና እህቶች የተውበትን ፀጋነት አስተውለን ይህንን ድንቅ የአሏህ ስጦታ እሱ ባዘዘን እንዲሁም መልዕክተኛው ( አለይሂ ሶላቱ ወሰላም) ባሳዩን መልኩ ልንጠቀምበት ይገባል እንጂ እንደ ቀልድ የምናስመልጠው እድል መሆን የለበትም።ከዚህ በተጨማሪ ተውበት ማለት ልክ እንደ ሶላት ፣ ፆም ፣ ዘካና መሰል የሆኑ ኢባዳዎች እራሱን የቻለ ዒባዳ መሆኑን ጠንቅቀን አውቀን በተገቢው መልኩ ልንፈፅመው ይገባል።
በመጨረሻም አሏህ
َّ (وَتُوبُوا إِلَى اللَّهِ جَمِيعًا أَيُّهَ الْمُؤْمِنُونَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ)
(ምእመናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ ።)
【አል—ኑር 31】
ብሏልና ይህንን የተከበረውን እንግዳ አድርሶን ፤ እሱ በሚፈልገው መልኩ ወደሱ በፀፀት ተመልሰው ይህንን ታላቅ ወር የሚቀበሉ እና በውስጡም መልካሙን ሁሉ ገጥሟቸው የውመል ቂያማ በፆማቸው አጅር ምክንያት ከሚደሰቱት ያድርገን ።
አሏሁመ አሚን!!
BY የቡታጅራ አህለሱና ቂራኣትና ዳዕዋ ቻናል
Share with your friend now:
tgoop.com/butajira_Qirat_daewa_group/1482