tgoop.com/coffeeandscribblings/626
Last Update:
ይህች ተራራማ ከተማ... ይህች ተራራማ ሀገር... ምስጢሯን መጠበቅ አታውቅበትም። ህንጻዎቿ ከዋክብት መስለው መብራታቸውን ያንቦገቡጋሉ። በተራ የተሰደሩ መዐት ከዋክብት። መኪኖቿ በተራሮቿ መቀነት ሽር እያሉ ከአይን ሲጠፉ እዚሁ ቁጭ ባልኹበት ይታየኛል።
ከላይ ከሚንቦገቦጉት ከተሞች ስር ጭል ጭል የሚሉ ኮሳሳ ቤቶች አሉ። ቡናማ ጣሪያቸው ቀለሙ ከማይለይ ግድግዳ ጋር። ነጭ ቲሸርት የለበሱ ባለነጫጭ ጸጉር አባወራዎች በዱካ የሚቀመጡባቸው። ትናንሽ ልጆች ፀጉራቸው እንደተንጨባረረ ቂጣቸውን ጥለው የሚሮጡባቸው። ሴቶች በሚዶ ጸጉራቸውን መንጨር መንጨር የሚያደርጉባቸው። ሳፋ፣ መዘፍዘፊያ፣ ጀሪካን፣ ሙቀጫ ደግሞ ሌላም ሌላም ዝርግፍግፍ ያለባቸው። ቢጫማ አፈራቸውን የለበሱ ግቢዎች። የተደጋገፉ ቤቶች። ጩኸት፣ ጫጫታ፣ እንቅስቃሴ የማይጠፋባቸው።
የአክስቴን ቤት ያስታውሱኛል። ወይም የሌላዋን። ወይም የእከሌን።
የሚብለጨለጩት መብራቶች ትናንሾቹን እንደሚውጧቸው አውቃለሁ። ፊት ለፊቴ የተዘረጋው የበቆሎ እርሻ አስፋልት እንደሚሆን አውቃለሁ።
አይቼዋለሁ። ስም ይቀየራል። ቦታ ይቀየራል እንጂ ታሪክ አይቀየርም።
ድህነት ሲያበሩት ወዴት ነው የሚሄደው? ክፉ ጥላውን ይዞ ፈንጠር ይላል እንጂ ይጠፋል?
ከአይን ቢርቅ ከልብ ይርቃል ድህነት?
የህጻናቱን ጩኸት እየሰማሁ አስባለሁ። የምብለጨለጨው የማንን ፋኖስ አጥፍቼ ነው?
@coffeeandscribblings
BY Coffee and Scribblings
Share with your friend now:
tgoop.com/coffeeandscribblings/626