tgoop.com/coffeeandscribblings/650
Last Update:
የማውቃቸው ቃላት ጠፍተውኝ ነው ወይስ ከድሮም የቃላት ሀብታም አልነበርሁም? የሚሰማኝን ስሜት ናፍቆት ብዬ ላሳንሰው አልችልም። ጣሽሀንብሱዝ የሚል ነገር ብዬ በአዲስ ቃል ልጠራው እፈልጋለሁ።
እዚህ አባት አያለሁ። በጎን እና በጎን ካኪ ወረቀት የሸጎጠ። ንጹህ ግን አርጀት ያለ ሱፉን ለብሶ።እግሮቹን ነጠቅ ነጠቅ እያደረገ፣ የጸሀይዋን ማቆልቆል እያየ ወደቤቱ የሚሮጥ። አየዋለሁ። አየዋለሁ። ግን የማየው እሱን አይደለም። አባቴን ነው። ጋሽ ጸጋዬን ነው። ጋሽ ተረፈን ነው። ደም እየመሰለች በምትጠልቅ ጸሀይ ወደቤት የሚገሰግሱ የሰፈሬን አባቶች ነው። ገብቶ በማላውቀው ቋንቋ እያወራ… የማላውቀውን ነገር… ለማላውቃቸው ልጆቹ እንደሚሰጥ አውቀዋለሁ። ግን የማየው የማውቃቸውን የሰፈሬን አባወራዎች ነው። ይሄ ምን ይባላል?ጣሽሀንብሱዝ ብለው ማን ይከሰኛል?
ሞተረኞች አያለሁ። በስራ ላይ። ሊያምታቱኝ ይሞክራሉ። ሊያደናግሩኝ። ከታሪፍ በላይ ሊያስከፍሉኝ። ይከራከሩኛል። ሳውቅባቸው ፈገግ ይላሉ። በላብ የወረዛ ፊታቸውን አያለሁ። ያልደላው እጃቸውን አያለሁ። የቆሸሸ ጫማቸውን አያለሁ።ሞተር ላይ ሲሆኑ የሚጎብጥ ጀርባቸውን አያለሁ። ግን የማየው የሀገሬ ታክሲ ረዳቶችን ነው። ጮኽ ብለው ሲጣሩ የሚወጠር አንገታቸውን ነው። በእጃቸው ሰብስበው የሚይዙትን የብር ኖት ነው። የሳንቲም ክምራቸውን ነው። በር ይመስል የማየው ሁሉ የሚከተኝ ወደሀገሬ ነው። ይሄ ምን ይባላል? ጣሽሀንብሱዝ ብለው ማን ይከሰኛል?
አንድ አይነት የለበሱ ልጃገረዶች አያለሁ። እንዲህ ያለ አለባበስ አላውቅም። መፍለቅለቃቸውን አያለሁ። ጉጉታቸው በፊታቸው ይታየኛል። ይንሾካሾካሉ፤ ይሳሳቃሉ። ሚዜ የሆኑ ይመስለኛል። አዲስ ልብስ እንደለበሱ ያስታውቃሉ። የሚታዩኝ የሀገሬ ልጃገረዶች ናቸው። ዘንጠው የማይጠግቡት። ታይተው የማይጠገቡት። ጠይምነታቸው የሚያበራ። በመንገድ እንደዚህ አይደለም የሚሆኑት? መስኮት ይመስል የማየው ሁሉ የሚያሳየኝ ሀገሬን ነው። ይሄ ምን ይባላል? ጣሽሀንብሱዝ ብለው ማን ይከሰኛል?
ህጻናት አያለሁ። ከየቤታቸው ወጥተው የተኮለኮሉ። ተንኮላቸው አያልቅም። ሳቃቸው አይጠገብም። የቆሸሹ ልብሶቻቸውን ያልተጸዳ ፊታቸውን ይዘው ያሳሳሉ። ላቅፋቸው ልስማቸው እመኛለሁ። የሚታዩኝ ግን እነአቤል ናቸው። መዐት ቤቢ የሚባሉ ልጆች። “ሰው ይለፍ አንተ።” ተባብለው እግር ኳሷቸው የሚያቆሙ። ስለሀገሬ አስባለሁ። እነዚህ ሰዎች ምንም ሳይበድሉኝ። ጣሽሀንብሱዝ ብል ማን ሀይ ባይ አለኝ?
ማን ይከለክለኛል?
@coffeeandscribblings
BY Coffee and Scribblings
Share with your friend now:
tgoop.com/coffeeandscribblings/650