tgoop.com/ethiopianarchitectureandurbanism/15086
Last Update:
“ ማንኛውም ሰው በተቋሙ ውስጥ አስፈላጊ የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶች ካላሟላ ከ10 ሺሕ ያላነሰ ከ100 ሺሕ ያልበለጠ ቅጣት ይጣልበታል ” - ኮሚሽኑ
የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶችን ባላሟሉ አካላት የገንዘብና የሥራ ፈቃድን እስከማሳገድ ቅጣትን የሚደነግግ ደንብ ማውጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ስጋት ሥራ አመራር አስታወቀ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው ደንቡ፣ “ማንኛውም ሰው በተቋሙ አስፈላጊ የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶች ሳያሟላ የቀረ እንደሆነ እንደ ደረጃው ከ10 ሺሕ ያላነሰና ከ100 ሺሕ ያልበለጠ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል” ይላል።
በኮሚሽኑ ደንብ መሠረት፦
ደንቡ፣ የህንፃዎችና የግንባታዎች ዲዛይን፣ ስለህንፃ፣ ግንባታና የግንባታ ሂደት መሟላት ያለባቸው የአደጋ ስጋት ደኅንነት መስፈርቶችንና የህንፃ አጠቃቀምን የተመለከቱ ግዴታዎችን አካቶ ይዟል።
የህንፃዎች ዲዛይን የሌሎች ሰዎችን ንብረቶች ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መሆን እንደሌለባቸው፣ በዲዛይኑ የእሳትና ሌሎች አደጋዎችን መከላከያና መቆጣጠሪያ መስፈርቶች መሟላት እንዳለባቸውም ደንቡ ያትታል።
ነባር ህንፃዎች ጥገና ወይም ለውጥ በሚደረግባቸው ጊዜ አደጋን ለመቆጣጠር/ለመከላከል የተገጠሙ ሲስተሞች ስለመሟላታቸው ፍተሻ ተደርጎ የአደጋ ደኅንነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መውሰድ ግዴታ መሆኑ ተመልክቷል።
በግንባታ ሂደት ያለ ህንፃ ሲጠናቀቅ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለሚያዙ ክፍሎች አስፈላጊ የደኅንነት ተግባራት መሟላታቸው ካልተረጋገጠ ለተጠቃሚዎች መተላለፍ እንደማይችልም በድንጋጌው ተጠቅሷል።
ህንፃ ተከራዮች አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ወይም ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የአደጋ ደኀንነት መስፈርቶችን እንዲያሟሉ፣ የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶችን ያላሟላ ነባር ህንፃ ባለቤት ለማሟላት የሚጠበቅበትን የማድረግ ግዴታ እንዳለበት በደንቡ ተገልጿል።
“ማንኛውም የጅምር ህንፃ ተጠቃሚ ከሚመለከተው አካል የመጠቀሚያ ፈቃድ መያዝ ይኖርበታል”ም ብሏል ደንቡ።
በተጨማሪም፣ አደገኛ ንጥረ ነገሮች የሚያከማቹ የሚያጎጉዙ፣ የሚጠቀሙ የደኀንነት የደኅንነት ብቃት ማረጋገጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ኮሚሽኑ የተከማቹ አደገኛ ንጥረ ነገሮችን እንደሚያስወግድ አትቷል።
እንዲሁም የተከለከሉ ድርጊቶችን ዝርዝር ያስቀመጠው ደንቡ የንግድ/የሥራ ፈቃድ እስከማሳገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚያስወስድ ገልጾ፣ እርምጃ አወሳሰድና አስተዳደራዊ ቅጣት ዝርዝር ድንጋጌዎችን ደንቡ አስቀምጧል።
ኮሚሽኑ ይህንኑ ደንብና ለማህበረሰቡ ሊቀርብ ስለሚገባ ግንዛቤ በተመለከተ ከሚዲያ ተቋማት የምክክር መድረክ ትላንት በሳሬም ሆቴል ያካሄደ ሲሆን፣ ተጨማሪ ይኖረናል።
(ሙሉ ድንጋጌ የያዘው ደንቡ ከላይ ተያይዟል)
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
BY Ethiopian Architecture Construction and Urbanism
Share with your friend now:
tgoop.com/ethiopianarchitectureandurbanism/15086