tgoop.com/ethiopianarchitectureandurbanism/15095
Last Update:
የወላይታ ሶዶ ከተማ የቶፖግራፊ ካርታ ዝግጅት
የወላይታ አውራጃ ካርታ እንዲነሣ እና የሰባቱ ወረዳዎች ይዞታ በካርታው ላይ እንዲሰፍር ካደረግሁ በኋላ፣ ለሶዶ ከተማ ዘመናዊ ማስተር ኘላን ወደ ማዘጋጀት ዕቅዴ ገባሁ፡፡ ለሶዶ ከተማ ዘመናዊ ማስተር ፕላን እንዲዘጋጅ ማድረግ የከተማዋ ዕድገት በዕቅድ እንዲመራ ያግዛል፡፡ ለዚህ ሥራ ደግሞ አስቀድሞ የቶፖግራፊ ካርታ መዘጋጀት አለበት፡፡ የቶፖግራፊ ካርታውን ለማዘጋጀት ሰርቬየሮች ከአገር ግዛት ሚኒስቴር የማዘጋጃ ቤቶች ክፍል እንዲሰጡኝ ብጠይቅ ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ለአስተዳደሩም ሆነ ለሕዝቡ አመች እንዲሆን አውራጃውን በአዲስ መልክ ለማዋቀር ከአገር ግዛት ሚኒስቴር ፈቃደኝነት ሳጣ፣ ቀደም ብሎ የአውራጃውን ካርታ በማንሳት ወደ ተባበሩኝ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ፊቴን አዞርኩኝና እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ የሥራ ሰዓት ሳይጠብቁና ቅዳሜ፣ እሁድ፣ የበዓል ቀን ሳይሉ፣ ለሶዶ ከተማ ማስተር አጠናቀቁልን፡፡ ባለሙያዎቹ የሕዝብና ቤት ቆጠራውን ስለአካሄዱልን እንዲሁም ፕላን ሥራ አስፈላጊ የሆነውን የቶፖግራፊ ካርታ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌሎች ብዙ የልማት ሥራዎችን በዕቅድ ለማከናወን የሚያስፈልገውንና ለልማት ሥራ መሠረት የሆነውን የአውራጃውንም ሆነ የሶዶ ከተማን ካርታ ስላነሱልንና ለወላይታ አውራጃ ልማት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ስላደረጉ ባለውለታዎች ናቸው፡፡ በጊዜው ምስጋና ያቀረብኩላቸው ቢሆንም እዚህ ላይ ስማቸው ሲጠራ እንዲኖር ደግሜ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ሥራውን አጠናቀው ሲያስረክቡንም አብረው የመሐንዲስ የሥራ መሣሪያዎችን ጭምር ለግሰውናል፡፡
#የመሐንዲስ የሥራ መሣሪያዎቹን ልገሳ ያደረጉልን፣ የውኃ ልማት መሥሪያ ቤት ሄጄ የካርታ ሥራ ባለሙያዎቹን ርዳታ በጠየኩበት ወቅት ከዕቃ ግምጃ ቤታቸው የመግባት እድል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ መሥሪያ ቤቱ በርዳታ ያገኛቸው ብዙ የቅየሳ መሣሪያዎች(ቴዎዶላይቶች፣ ጃሎዎች፣ ስታድያዎችና ባለመቶ ሃምሳና ሰላሳ ሜትር፣ አደጋ የሚችሉ እና ለገጠር ሥራ አገልግሎት የተሠሩ ጥቅል ሜትሮች) የዕቃ ግምጃ ቤቱን ያጨናነቁት መሆኑንም አይቼ ነበር፡፡ ስለዚህ የውሀ ልማት ባለሙያዎች ወደ አውራጃው ይዘዋቸው የሄዱትን የቅየሳ መሣሪዎች እዛው ለአውራጃው ግዛት ለልማት ሥራ አገልግሎት እንዲውሉ፣ ያንበሳ ልመና ጋማ ይዞ እንደሚባለው ሆኜ ሥራው ሲያልቅ መሣሪያዎቹን ሁሉ ትተውልን እንዲሄዱ አድርጌያለሁ፡፡
#የባለሙያዎቹ ኃላፊ የነበረው ስሙን የዘነጋሁት መሐንዲስ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ባየኝ ቁጥር «ባገለገልን ፈንታ መሣሪያዎቻችንን ነጥቀህ አባረርከን›› እያለ በውስጠ ወይራ ቀልድ እየወቀሰኝ እንሳሳቅ ነበር፡፡ የቅየሳ መሣሪያዎቻቸውም በወላይታ አውራጃ ለወረዳ ከተማዎች መንገዶች ቅየሳ እንዲሁም በአበላና በሌ ለሰፈሩት ጭሰኞች ለአንድ ሰው አምስት ሄክታር (250 በ200 ሜትር) መሬት እየሸነሸኑ ለመስጠት አገልግለውናል፡፡ በተጨማሪም የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ በነበርኩበት ጊዜ ከዲላ እስከ ሞያሌ : ባለው ኢንተርናሽናል መንገድ ላይ ላሉ ከተሞች ቶፖግራፊ ካርታ ለማዘጋጀት ለቅየሳ ሥራ ተጠቅመንባቸዋል፡፡ የውኃ ልማት መሥሪያ ቤት በባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን በቅየሳ መሣሪዎችም ርዳታ ስላበረከተልን ከፍ ያለ ምስጋና ይገባዋል፡፡
▼ሕይወቴ ፤ ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ ፣ 262-3
Via Ethiopian History and Tourism/የኢትዮጵያ ታሪክና ቱሪዝም
@ethiopianarchitectureandurbanism
BY Ethiopian Architecture Construction and Urbanism
Share with your friend now:
tgoop.com/ethiopianarchitectureandurbanism/15095