tgoop.com/ewuntegna/11895
Last Update:
ዘመነ በርዮድ ጳጕሜን
ዓመትን በዘመናት ስንከፋፍለው በ4ት ዘመናት ይከፈላል፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ዘመነ ክረምት (ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25) ነው፤ በዘመነ ክረምት ውስጥ ደግሞ ከሚውሉት መካከል ከነሐሴ 28 እስከ ጳጕሜን ፭ት (በሠግር ዓመት ፮ት) ድረስ ያለው #ዘመነ_በርዮድ_ ይባላል፤ ይህም ወደ አዲስ ዘመን የሚያሻግረን ነው፡፡ በቅዱስ ያሬድ ድጓ መሠረትም ጎሕ (ውጋገን)፣ ነግህ (ንጋት)፣ ጽባሕ (ጥዋት)፣ ብርሃን፣ መዓልት (ዕለት)፣ ጌና (ልደት) ይባላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም (ዘመንን ቀንን በቊጥር ሰጣቸው፣ በውስጧም ያለውን ፍጥረት አስገዛቸው፡፡) እንዲል [ሲራክ 17፥2]
ጳጕሜን ማለት ጭማሪ ማለት ነው፤ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት በስድስት መቶ ዓመት አንዴ ደግሞ ሰባት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ ጳጕሜን በአራት ዓመት አንዴ (ማለትም በዘመነ ሉቃስ መጨረሻ በዘመነ ዮሐንስ ቅበላ ስድስት ቀን ትሆናለች)፤ የአለፈውን የ2011 ዓ..ም ወርኀ ጳጕሜን ማስታወስ ግድ ነው፡፡ በዚህም ሃገራችን ኢትዮጵያ የዐሥራ ሦስት ወራት ጸጋ /Thirty months of sunshine/ በመባል ትታወቃች፡፡
የጳጕሜን ጾም ጾመ ዮዲት
በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጕሜን ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም በተጨማሪ ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፤ ጾሙ እንደ ጾመ ጽጌ የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ጾመ ዮዲት የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ /እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡/ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉሥ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ፥ ድንበር አስፋ፤ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ፥ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ [ዮዲት 2፥2-7]፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋት በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡
ዮዲት ባሏ ሞቶባት፤ ከወንድ ርቃ፥ ንጽሕናዋን ጠብቃ፥ በጾም፥ በቀኖና፥ በሐዘን ተወስና የምትኖር ነበረችና፤ በተፈጠረው ጥፋት ሕዝቡ ላይ ለመጣው መከራ፤ ማቅ ለብሳ፥ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክን ሕዝቡ የሚድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለጸላት [ዮዲት 8፥2] ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንንና ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን ለመጎናጸፍ ጳጕሜን በፈቃድ እንጾማለን፡፡
ጳጕሜን የዕለተ ምጽአት መታሰቢያ
የጳጕሜን ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጕሜን የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ፤ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ፥ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡
ጠበል በወርኀ ጳጕሜን
ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጕሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጠበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን ነው፡፡ የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጠበል ደግሞ ከበሽታችን ያድነናል፥ የተቀደስንም ያደርገናል፤ መጪውንም ሕይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ከ/የቀጨኔ ደ/ሰላም መድኀኔ ዓለምና ደ/ት/ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ/ት/ቤት/
@ewuntegna
@ewuntegna
BY ተአምረ ማርያም ✤የእመቤታችን ተአምር የሚነገርበት✤ የቅዱሳን ህይወት የሚተረክበት
Share with your friend now:
tgoop.com/ewuntegna/11895