tgoop.com/ewuntegna/11981
Last Update:
+ አንገት ተቆርሶ የተከበረ ልደት +
በመጽሐፍ ቅዱስ ልደት ያከበሩት የግብፁ ንጉሥ ፈርዖንና የይሁዳው ገዢ ሄሮድስ ናቸው:: እርግጥ ነው ልደትን ማክበር በአሕዛብ ነገሥታት ቢዘወተርም የሚነቀፍ ነገር አይደለም:: ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስም የሚጀምረው የሰማይና የምድርን ልደት በሚተርከው "ኦሪት ዘልደት" ነው::
"እግዚአብሔር አምላክ፥ ሰማይንና ምድርን ባደረገ ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ፥ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው" (ዘፍ. 2:4)
ትልቅዋ አፈር መሬት በሰባት ዓመት ማረፍዋን አይተን እኛም በሰባት ቀን እንደምናርፍ የምድርን ልደት መተረክ አይተን ልደታችንን ብናከብር ክፋት የለውም:: (Microcosm /ንዑስ ዓለም/ እንዲል ቴዎሎጂ) የመድኃኔዓለምን ልደት ከፍ አድርገን የብዙ ቅዱሳንን ልደት ደግሞ እንዲሁ በቤተ ክርስቲያን ማክበራችን ልደት አንዱ እግዚአብሔርን ማመስገኛ ቀን ስለሆነ ነው:: ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አንዳንዶቹ ደግሞ የልደቴ ቀን ብለው የሚያከብሩት ለዳግም ልደት ክርስትና የተነሡበትን ቀን ነው::
በዛሬው ዕለት ሔሮድስ ያከበረው ልደት ግን እጅግ የተረገመው ልደት ነበር:: ተጋባዦቹ የንጹሕን ሰው ደም የጠጡበት ልደት ሔሮድያዳ እንደ ታላቂቱ ባቢሎን "በሰማዕቱ ደም ሰክራ" የዋለችበት የልደት ግብዣ ቀን ነበር::
በዚህ ልደት የተቆረሰው ኬክ አይደለም:: በዚህ ልደት እፍ ተብሎ የጠፋው ሻማ አይደለም:: በሰይፍ ተቆርሶ በሰሃን የቀረበው ከሴት ከተወለዱት ሁሉ የሚመስለው የሌለ ቅዱስ ሰው አንገት ነበር:: በሻማ ፈንታ የጠፋው ክርስቶስ "እርሱ የሚያበራ መብራት ነበር እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ" ብሎ የተናገረለት መብራት ቅዱስ ዮሐንስ ነበር:: እርግጥ ነው በልደት ሰበብ ብዙ ኃጢአት ይሠራል:: በሔሮድስ ልደት ግን የተሠራው ግፍ ዓለምን የሚያንቀጠቅጥ ግፍ ነው::
ሔሮድስ የገደለው ማንን ነው? ነቢይን ነውን? እውነት እላችኁዋለሁ ከነቢይ የሚበልጠውን ነው:: ከሴት ከተወለዱት ሁሉ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም:: አንድን ሰው ብቻ የገደለ መስሎታል::
እርሱ የገደለው ዓሥር ሰው ነው:: ከነቢያት የመጨረሻውን ነቢይ ከሐዋርያት የመጀመሪያውን ሐዋርያ ገደለ:: ለብዙዎች የንስሓ ሰባኪያቸውን ለብዙዎች አጥማቂያቸውን ገደለ:: መለኮትን ያጠመቀውን ወደር ያልተገኘለትን አጥማቂ ገደለ::
አንገቱ ተቀልቶ ለሚያይ ወንጀለኛ ይመስለዋል እርሱ ግን ብቻውን በበረሓ የኖረ ባሕታዊ ነበረ:: ጮማ ያቆረጠ ጠጅ ባፉ ያልዞረ በልብስ ያላጌጠ ሰውነቱን በኃጢአት ያላሳደፈው መናኝ በዚያች በተረገመች የልደት ቀን አንገቱ በሰሐን ቀረበ::
የሐዲስ ኪዳኑ ናቡቴ ሕገ እግዚአብሔርን ርስት አድርጎ በኤልዛቤዋ ሔሮድያዳ ምክር በሔሮድስ ትእዛዝ ተገደለ:: የሐዲስ ኪዳኑ ኦርዮ የሔሮድስን አመንዝራነት ለመደበቅ በግፍ ተገደለ:: ዳዊት ኦርዮን ባስገደለ ጊዜ በእጅ አዙር አደረገው እንጂ በፊት ለፊት አላደረገውም:: በኁዋላም ዕድሜውን ሙሉ አልቅሶአል:: ሔሮድስ ግን ኀዘኑ የለበጣ ነበረ::
ቅዱስ ያሬድ “ቢበላው ይሻላል” ባለለት መሐላው አሳብቦ ታላቁን ነቢይ አንገቱን ቀላው:: ቅዱስ ኤፍሬም "አዳምን በጎኑ አጥንት በሔዋን ድል የነሣው ሰይጣን ሔሮድስን በጎኑ አጥንት በሔሮድያዳ ድል አደረገውና ቅዱሱን ዮሐንስ ገደለው" ይላል::
በቤተ መንግሥቱ መካከል የዮሐንስ አንገት እንደ ምግብ በሳሕን ይዘሽ ለእናትሽ ያቀበልሽ አንቺ ሴት ምንኛ ብትረገሚ ይሆን:: በምድረ በዳ የጮኸ አፉን ክፉ ያላዩ ዓይኖቹን ምላጭ ያልነካው ጠጉሩን በሳሕን ላይ ይዘሽ ስትሔጂ ምን ተሰምቶሽ ይሆን?
መጥምቁን በመግደል ኃጢአትን መሸፈን አይቻልም:: ቅዱስ ኤፍሬም "የዮሐንስ ራስ የገዳዮቹን ኃጢአት አጉልቶ የሚያጋልጥ መብራት ነበረ:: ዮሐንስ በቃሉ ከተናገረው በላይ በሞቱ ኃጢአታቸውን ከፍ አድርጎ አሳየ" ይላል::
ክፋታቸውን ለመደበቅ እንደ ሔሮድስ ንጹሐንን የሚያስሩ : የልባቸውን ሠርተው በሞተ ጊዜ የውሸት የኀዘን መግለጫ የሚሠጡ ሁሉ መጨረሻቸው ዕብደት ነው:: ከማንም በላይ የሟች ደም የሚጮኸው በገዳይ ሕሊና ውስጥ ነው::
ሔሮድስ ዮሐንስ ገድሎ ተረበሸ:: አይሁድ ጌታ ለመነሣቱ ብዙ ምስክር ቀርቦላቸው ያላመኑትን እርሱ ግን ያለ ማስረጃ "መጥምቁ ዮሐንስ ተነሥቶአል" ብሎ መዘላበድ ጀመረ::
ዮሐንስን በሰይፍ መቅላትና ስብከቱን ዝም ማስባል የሚቻል መስሎት ነበር:: ዮሐንስ ግን ሰማዕት ሲሆን በገዳዩ ሔሮድስ ልብ ውስጥ ስብከት ጀመረ:: እኛ ቆመን ስንለፈልፍ አንሰማም ዮሐንስ ግን ሞቶ ገዳዩን አስጨነቀ:: ነቢዩ ኤርምያስን ጉድጉዋድ የጣለው ንጉሥ ጳስኮርን :- ከእንግዲህ ስምህ ማጎርሚሳቢብ ነው ለራስህና ለወዳጆችህ ፍርሃት አደርግሃለሁ እንዳለው የመጥምቁ ገዳዮች ገድለን አረፍን ሲሉ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ፍርሃት ሆኑ:: ንጹሐንን መግደልና በሞታቸው መሳቅ ይቻላል:: የደማቸውን ድምፅ ግን ከራስ ከሕሊና ማጥፋት አይቻልም:: አሁንም እንላለን ከሟች በላይ ገዳይ ያሳዝናል::
( በ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ )
@ewuntegna
@ewuntegna
BY ተአምረ ማርያም ✤የእመቤታችን ተአምር የሚነገርበት✤ የቅዱሳን ህይወት የሚተረክበት
Share with your friend now:
tgoop.com/ewuntegna/11981