tgoop.com/ewuntegna/13299
Last Update:
ጽዮንን የሚጠሉ ኹሉ ይፈሩ (፻፳፰፥፭)
(በዲ/ን ናትናኤል ግርማ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ደቀመዝሙር) ኅዳር 20ቀን 2017 ዓ.ም
እስራኤል ከግብፅ ከባርነት ከወጡ በኋላ ጸልየው እንዲድኑባት ሰውተው እንዲከብሩባት ታቦተ ጽዮንን ሰጥቶቸዋል:: በታቦተ ጽዮን እየተማፀኑ አርባ ዘመን ደመና እየጋረደ መና እያወረደ ዐለት እየሰነጠቀ ውኃ ከጭንጫ እያፈለቀ በሰላም ተንከባክቦ መግቦ ምድረ ርስት አግብቷቸዋል። ከዚህም በኋላ መስፍን ሲሞት መስፍን ካህን ሲሞት ካህን እየተተካ ሥርዓቱ ሳይጓደል ከዔሊ ደረሰ። ዔሊም ክህነት ከምስፍና አስተባብሮ ይዞ ዐርባ ዘመን ካስተዳደረ በኋላ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ልጆቹን ከበታቹ ሾማቸው። ጌታን የሚያስቆጣ ሦስት ዐበይት ኀጣውእ ሠርተዋል:: ነህ ፱ ፥ ፳፩፣ የሐዋ ሥራ ፲፫ ፥ ፲፰
አባታቸው ዔሊ ይህን ሰምቶ ‹‹ደቂቅየ እኮ ሠናይ ዘእሰምዕ ብክሙ ለእመ አበስ ሰብእ ላዕለ ቢጹ አምኃበ እግዚአብሔር ይጼልዩ ሎቱ:: ልጆቼ ስለእናንተ የምሰማው ደግ አይደለም፣ ሰው ሰውን ቢበድለው በእግዚአብሔር ያስታርቁታል፤ ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል ግን በማን ያስታርቁታል? ተዉ አይሆንም አላቸው:: ዳሩ ግን ከጌታው ይልቅ ለልጆቹ አድልቶ ልሻራቸው ሳይል ቀረ። ፩ኛ ሳሙ ፪ ፥ ፳፭
ታቦተ ጽዮንን እያገለገለ የሚኖር ሳሙኤል በዚያች ሌሊት ተኝቶ ሳለ ጌታ ‹‹ሳሙኤል ሳሙኤል›› ብሎ ጠራው። ዔሊ የጠራው መስሎት ሄዶ ‹‹ነየ ገብርከ ዘጸውዐከኒ›› እነሆኝ የጠራከኝ አለ፡፡ አልጠራሁህም ሔደህ ተኛ አለው፤ ኹለተኛ ጠራው፤ ከዔሊ ቀረበ ዒሊ ይህ ብላቴና ራእይ ተገልጾለት ይሆናል ብሎ እንግዲህ ወዲህ ቢጠራህ ተነሥተህ ታጥቀህ እጅ ነሥተህ ቁምና እነሆ ባርያህ እሰማለሁ ተናገር በል አለው። ሦስተኛ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ተነሥቶ ታጥቆ እጅ ነሥቶ ቆመና ባሪያህ እሰማለሁና ተናገር አለ፡፡ ልጆቹን ከመበደል አልከላከላቸውምና እንድፈርድበት የተናገሩኩትን በዔሊ እፈጽምበታለሁ ብሎ የእስራኤልን መመታት የታቦተ ጽዮንን መማረክ የአፍኒን ፊንሐስን የዔሊን ሞት ነገረው፡፡ ሲነጋ ዔሊ እግዚአብሔር የነገረህን አንዳችም ሳታስቀር ንገረኝ አለው፤ ነገረው። ዔሊም ‹‹ለይግበር እግዘአብሐር ዘአደሞ›› እርሱ እግዚአብሔር ነው የወደደውን ያድርግ አለ፡፡
ጌታ የማያደርገውን አይናገርም የተናገረውን አያስቀርምና እስራኤል በኢሎፍላውያን ዘምተው በአንድ ጊዜ አራት ሺህ ሰው አለቀባቸው። ይህ ነገር የሆነብን ታቦተ ጽዮንን ባለመያዛችን ነውና ታቦተ ጽዮንን ላክልን ብለው ወደ ዔሊ ላኩ። አፍኒን ፊንሐስ ታቦተ ጽዮንን ይዘው ሄዱ። በእስራኤል ጦር ሰፈር ታላቅ ደስታ ተደረገ ዕልልታው ደመቀ:: ኢሎፍላውያን ድል ያደረግን እኛ ነን እነሱ ምን አግኝተው ነው የሚደሰቱት አሉ፤ በታቦተ ጽዮን ምክንያት መሆኑን ሲያውቁ በግብጻውያን የሆነውን ሰምተዋልና ወዮልን ወዮልን አሉ።
ኋላ ግን ተጽናንተው ገጠሙ። እስራኤል ተመቱ አፍኒን ፊንሐንስ ሞቱ ታቦተ ጽዮንም ተማረከች፤ አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀዶ አመድ ነስንሶ ወደ ከተማ ተመለሰ። የኀዘን ምልክት ነው፤ ከዚያም ታቦተ ጽዮን እንደተማረከች፤ ካህናቱም እንደሞቱ፤ ሕዝቡም እንደተሸነፉና ብዙ ሕዝብ እንዳለቀ ለከተማው ሁሉ አወራ፤ ከተማዋ በልቅሶና በዋይታ ተናወጸች፣ በዚህ ጊዜ ዔሊ የዘጠና ዓመት ሽማግሌ ነበርና የሆነውን ሰምቶ ደንግጦ ከመንበሩ ወድቆ የጎድን አጥንቱ ታጥፎ ሆዱን ወግቶት ሞቷል። ፩ኛ ሳሙ ፬ ፥ ፱
ፍልስጥኤማውያንም ታቦተ ጽዮንን አዛጦን ወስደው በቤተ ጣዖታቸው ከዳጎን ጋር አስቀመጧት። በማግሥቱ ሊያጥኑት ቢገቡ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በግምባሩ ወድቆ አገኙት፤ ከቦታው መልሰውት ሄዱ። በማግስቱ ሲመለሱ እጅ አግሩ ተቆራርጦ ደረቱ ለብቻው ቀርቶ አገኙት፣ ሰዎቹም በአባጭ ተመቱ። መቅሠፍቱ ቢጸናባቸው ወደ ጌት ወስዷት፤ የጌት ሰዎችም እንዲሁ በመቅሠፍት ተመቱ ወደ አስቀሎና ቢወስዷት ልታስፈጁን ነውና መልሱልን አሏቸው፡፡ ከሰባት ወር በኋላ ወደ ሀገሯ ትመለስ ብለው ቀንበር ባልተጫነባቸው በሚጠቡ ላሞች በሚሳብ አዲስ ጋሪ አድርገው የበደል መስዋእት እንዲሆን በአምስቱ ከተሞቻቸው አምሳል አምስት የወርቅ አይጦች አድርገው ሰደዷት። ላሞቹም ወደ ግራ ወደ ቀኝ ሳይሉ ቤተ ሳሚስ ከኢያሱ እርሻ ደርሰው ቆመዋል። ታቦተ ጽዮንን ከሐውልተ ስምዕ አኑረው ሠረገላውን ፈልጠው ላሞቹን አርደው አወራርደው መስዋዕት አቀረቡ፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ታቦተ ጽዮንን በድፍረት በማየታቸው ከመካከላቸው አምስት ሺህ ያህሉ ተቀሰፉ፤ ፈርተው ታቦተ ጽዮን መጥታለችና ውሰዱ ብለው መልእክተኛ ላኩ:: ወስደው በአሚናዳብ ቤት አድርገዋት ልጁ አልዓዛር ኻያ ዓመት አገልግሏታል። ፩ኛ ሳሙ ፯ ፥ ፪ እስራኤል ታቦት ጽዮንን ከጠላት ሲታደጉባት ከአባር ከቸነፈር ሲድኑባት ከእግዚአብሔር ጋር ሲታረቁባት በረከትና ረድኤት ሲቀበሉባት እስከ ሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ድረስ ኖረዋል። በሰሎሞን ዘመነ መንሥት እስራኤል ወደ ፊት ጠፍ እንደምትሆን እግዚአብሔር ስለሚያውቅ በእርሱ ቸርነት በሰሎሞን አስረካቢነት በቀዳማዊ ምኒልክ ተረካቢነት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ችላለች:: እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በአክሱም ትገኛለች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ጽዮን የሚለው ቃል ለዐምስት ነገሮች ይቀጸላል! ጽዮን የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ፀወን አምባ መጠጊያ ጥላ ከለላ ማለት ነው። ጽዮን የሚለው ቃል ለዐምስት ነገሮች መጠሪያ ሆኗል። እነዚህም፦
፩. ሙሴ በደብረ ሲና ከእግዚአብሔር የተቀበለው ጽላተ ሕግ፤ ጽላተ ሙሴ ወይም ታቦት ጽዮን ትባላለች። ፩ኛ ሳሙ ፪ ፥ ፲፱
፪. የአብርሃም ርስት የኾነችው ኢየሩሳሌም ጽዮን ትባላለች! ፪ኛ ሳሙ ፭ ፥ ፮
፫. ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጽዮን ቅድስት ትባላለች፤ ‹‹ነያ ሠናይት ሰላማዊት ጽዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አፍላገ ሕይወት በየማና ወበጸጋማ አዕፁቀ ዘይት ኵለንታሃ ወርቅ ወያክንት ሀገሮሙ ለሰማዕት᎓᎓›› የሰማዕታት ሀገራቸው ሁለንተናዋ በወርቅና በዕንቍ የተሸለመች በቀኟ የሕይወት ወንዞችን በግራዋ የዘይት ልምላሜዎችን የያዘች ሰላማዊት አምባ መጠጊያ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እነሆ ያማረች የተወደደች ናት።› ብሏል ሊቁ ቅዱስ ያሬድ።
፬. መንግሥተ ሰማያት ደብረ ጽዮን ትባላለች አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው መንግሥተ ሰማያት ደብረ ጽዮን ተብለ እንደምትጠራ ‹‹ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን እለ ተጋባእክሙ በዛቲ ዕለት ከማሁ ያስተጋባእክሙ በደብረ ጽዮን ቅድስት ወበኢየሩሳሌም አግዐዚት በሰማያት᎓᎓›› የክርስቲያን ወገኖች በዚች ዕለት እንደተሰበሰባችሁ፤ ነጻ በምታወጣ በደብረ ጽዮን በመንግሥተ ሰማያት ይሰብስባችሁ በማለት ይመሰክራል።
፭ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም፤ ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ‹‹አብርሂ ጽዮን ዕንቁ ዘጳዝዮን ዘአጥረየኪ ሰሎሞን። ዕዝራኒ ርእያ በርእየተ ብእሲት ጽዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ የዓውዳ ስብሐት።›› ሰሎሞን ጳዝዮን በሚባል ዕንቊ የተወዳጀሽ ጽዮን ሆይ አብሪ፣ ዕዝራም ምስጋና የሚከባት የክርስቲያን ማደሪያ የሆነች ቅድስት ጽዮንን በሴት አርአያ አያት። በማለት ሰሎሞንና ዕዝራ በአንድ መንፈስ ሆነው ስለ እመቤታችን ተቀኝተዋል። ጽዮን የሚለውን ቃል ከእመቤታችን ጋር ያለውን ተዛምዶ በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡ የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ የኾነችው በወርቅ የተለበጠችው ይቺ የእግዚአብሔር ታቦት፣ በንጽሕና በቅድስና የተጌጠችው የእግዚአብሔር ወልድ እናት የኾነችው የአማናዊት ታቦት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡
BY ተአምረ ማርያም ✤የእመቤታችን ተአምር የሚነገርበት✤ የቅዱሳን ህይወት የሚተረክበት
Share with your friend now:
tgoop.com/ewuntegna/13299