tgoop.com/ewuntegna/14149
Last Update:
ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሠሉስ
ለምስጋና ሁለተኛ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን ነው በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል፡፡ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል ከዚያ ላይ ሁኖ ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ አፍሬም ትለዋለች : እርሱም ታጥቆ እጅ ነስቶ ይቆማል፡፡ ወድስኒ ትለዋለች በዕለት ሰኑይ ክርክር አልቋልና ባርከኒ ይላታል፣፣ በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ ይኅድር በላዕሌከ ትለዋለች፡፡ ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል፡፡ ውዳሴ ዘሠሉስ ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ሠሉስ ይላል ቃለ ጸሓፊ ነው፡፡ እርሱ ግን አክሊለ ምክሕነ ብሎ ይጀምል፡፡
አክሊለ ምክሕነ፡፡
አክሊል የወዲህኛው ፤ ምክሕ የወዲያኛው::
ወቀዳሚት መድነኒትነ፡፡
ቀዳሚት የወዲህኛው ፡ መድኃኒት የወዲያኛው።
ወመሠረተ ንጽሕነ፡፡
መሠረት የወዲህኛው፤ ንጹሕ የወዲያኛው፡፡
ኮነ በማርያም ድንግል።
በማርያም ድንግል ሆነልን አለ፡፡ ማርያም ናት ሲል ነው፡፡ አንድም በዚህ ቀን ከነገሥታት ዳዊትን ፤ ከመሳፍነት ኢያሱን ፤ ከደናግል ኢሊያስን አስከትላ መጥታለች፡፡ ዳዊት ምንም ንጉሠ ነገሥት ብትባል የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻልህም፡፡ ኢያሱም መድኃኒት ብትባል የድኅነታችን መጀመሪያ መሆን አልተቻለህም፡፡ ኤሊያስም ንጹሕ ድንግል ብትባል ፣ የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልተቻለህም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ የድኅነታችን መጀመሪያ ፤ የንጽሕናችን መሠረት ድንግል ማርያም ናት ሲል ነው፡፡ አንድም አክሊሎሙ ለሰማዕት እንዲለው አክሊለ ሰማዕት የሚባል ጌታ፡፡
ጥንተ ሕይወቶሙ እንዲለው ጥንተ ሕይውት የሚባል ጌታ አኃዜ ዓለም በአራኈ ኩሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ መሠረት ዓለም !ይጸውር ድደ ወይነብር ፈረ እንዲል፤ መሠረተ ዓለም የሚባል ጌታ ፣ በድንግል ማርያም ተሰማልን፡፡ ትላንት ስሟን አላነሳም ዛሬ ስሟን አነሣ በአንግዳ ልማድ እንግዳን ዕለቱን ስሙን እየጠሩትም ፣ ከዋለ ካደረ በኋላ ስሙን ይጠሩታል በዚያ ልማድ ፣ ማርያም ማለት ፍጽምት ማለት ነው : ለጊዜው መልክ ከደም ግባት አስተባብራ ተግታለች፡፡ ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡
አንድም ጸጋ ወሀብት ማለት ነው ለጊዜው ለናት ላቲ ጸጋ ሁና ተስጥታለች ፍጻሜው ግን ለሰው ሁላ ጸጋ ሁና ተስጥታለችና አንድም መርሕ ለመንግስተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ምእመናን መርታ ገነት መንግስተ ሰማያት አግብታለችና::
አንድም ልዕልት ማለት ነው፡፡ ሮም አርያም ማለት ልዑል ማለት እንደ ሆነ፡፡ እርሷንም መትሕተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ይላታልና፡፡ አንድም ማኅበረ መሐይምናን ሕዝብ ተለአኪተ እግዚአብሔር ወሰብእ ተፈሥሒ ቤተ እስራኤል ፤ ወተሐሰዩ ቤተ ይሁዳ ማለት ነው፡፡ አንድም ማርያም ማለት እግዝእተ ብዙኃን ማለት ነው፡፡ አብርሃም ማለት አበ ብዙኃን ማለት እንደሆነ፡፡
እንተ ወለደት ለነ ዘእግዚአብሔር ቃለ፡፡
መመኪያነቷን በቅጽል አመጣው አካላዊ ቃልን በወለደች በድንግል ማርያም ተገኘልን፡፡
እኛን ስለማዳን ሰው የሆነ፣፣
ዘኮነ ሰብእ በአንተ መድኃኒትነ፡
እምድኅረ ኮነ ሰብአ ጥዩቀ አምላክ ፍጹም ውእቱ፡፡
ሰውም ከሆነ በኋላ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ሐራ ጥቃቃል ሥጋ ኮነ ያለውን ይዘው ወደ ታች ተለወጠ ይላሉና ሰውም ከሆነ በኋላ ፍጹም አምላክ ነው አለባቸው::
ስለዚህ ነባር ማኅተመ ድንግግልናዋ ሳይለወጥ ወለደችው፡፡
ወበእንተዝ ወለደቶ እንዘ ድንግል ይእቲ፡፡
መንክር ኅያለ ወሊዶታ ዘኢይትነገር፡፡
ድንቅ የሚሆን የመውለዷ ሥራ የማይመረመር ነው፡፡ የማይመረመር የመውለዷ ሥራ ድንቅ ነው፡፡
ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡
በማይመረመር ግብር ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ስርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡አይምዕሮውን ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን::
@ewuntegna
@ewuntegna
BY ተአምረ ማርያም ✤የእመቤታችን ተአምር የሚነገርበት✤ የቅዱሳን ህይወት የሚተረክበት
Share with your friend now:
tgoop.com/ewuntegna/14149