tgoop.com/eyorkis/1284
Create:
Last Update:
Last Update:
አንቺን ልጠብቅሽ
እንዴት ብየ ልይሽ
ስሚኝ የኔ እመቤት
የሳሎኔ ውበት
የሕይወቴ ድምቀት
በአካል ላላገኝሽ በርሃው አይሏል
ከየብሱ ለጥቆ ባህሩ ተኝቷል
ባህሩ ቢታለፍ አድማስ ተዘርግቷል
እንዴት ብየ ልኑር አይንሽን ሳላየው
በሃሳብ ሸራ ላይ ገላሽን እያየው
እንዴት ልንቋቋመው የናፍቆትን በትር
በምን ልሻገረው የለየንን ድንበር ?
መቸም እጅ አልሰጠም
መቸም ተስፋ አልቆርጥም
አይገድልም ህመም ነው የናፍቆት ውሃ ጥም
ተስፋ መቀመር ነው ተራርቆ ፍቅር
ፈንድቶ የማይለይ በልብ ውስጥ የሚቀር
ታዲያ እንዴት ልይሽ?ድንበሩን አልፌ ባህሩን ቀዝፌ
ከሃሳብ እንድድን ገላሽን አቅፌ
ጀምበር ገባች ፥ መሸ
ያጸዳሁት ቤቴም ፥ መልሶ ቆሸሸ
አልጠፋም መብራቱ
አልተበላም 'ራቱ
አሁንም ክፍት ነው በርና መስኮቱ ።
ለቁር ተጋለጠ ፥ ጓዳዬ እንደ ውጪው
መቼ ነው የምትመጪው ?
መጽሐፍ ገለጥኩና መልሼ ዘጋሁት
ልጽፍ አሰብኩና ብዕሬን ወረወርኩት
መቆም መንጎራደድ
መቆም መንጎራደድ
መቆዘም መተከዝ ፥ በሐሳብ መሰደድ
ደርሶ ብንን ብንን
ደሞ ቁጭ ብድግ
ካንቺ ውጭ አላውቅም ምን እንደምፈልግ ።
ምኞት ነው ያለኝ ፥ ዝም ብሎ ምኞት
ወይ የማያኖር ፥ ወይ የማያስሞት
ትመጫለሽ እያልኩ በጉጉት ከምኖር
ምናለ በሞትኩኝ ለአንድ ለስድስት ወር ።
BY ኢዮርቅስ

Share with your friend now:
tgoop.com/eyorkis/1284