tgoop.com/fnoteAemro/263
Last Update:
✞ የወሲብ ፊልምና ጠንቆቻቸው ✞
ክፍል - 3
በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን፡፡
✞ የወሲብ ፊልም የቱን ያህል በዘመኑ ፋሽን ዘልቆ ሄደ? ✞
የዝሙት ፊልሞችና ምስሎች በዓለም አህጉራት በከፍተኛ ደረጃ የመሰራጨታቸው ሚስጢር ከጀርባው በተቀናጀ አደረጃጀትና ህቡዕ በሆነ አካሄድ ውስጥ የተሰለፉ የሚስጢር ማኅበራት ተጽዕኖ እና አቅም አማካኝነት ነው፡፡ አብዛኛው የወጣቱ ትውልድም በቀላሉ በሚያገኘው የእጅ ስልኮቹና የመገናኛ አውታሮች በኩል የሚለቀቁት እነዚህ የርኩሳን መናፍስት አዚማዊ መሣሪያ የሚሆኑ ፊልሞች፤ ወደኑሮና ልማድ የመቀላቀል ፍጥነታቸው ከፍተኛ የሆነ ሲሆን ያለ ውጣ ውረድና ተጨማሪ ጉልበት የተፈጥሮ ስሜት ላይ በመመርኮዝ የአእምሮ ክፍልን ተቆጣጥሮ በፍላጎት ስሜት አነሁልሎ በማደንዘዝ ወደ ልክፍት የሚመራ ስውር የማይነገርለት ጠፍናጊ ሱስ የመሆን ባሕሪይ ያለው የክፍለ ዘመናችን ማፍዠዣና ትውልድን ማሰሪያ ወጥመድ ነው፡፡
+++
ፊልሞቹ በጥንቃቄ ታቅደው ሲዘጋጁ ከኋላቸው እንዲያሳኳቸው የተቀመጡላቸው መናፍስታዊ ራእይና ግብ አላቸው፡፡ ከነዚያም መካከል ትውልዱ በሚከተላቸው የፋሽን፣ የአለባበስ፣ የመዝናኛ እና ሌሎች ዘርፎች በኩል ተዘዋዋሪ የሚመስል ነገር ግን በቀጥታ የተቆራኘ ዲያቢሎሳዊ ስብከቶችንና መገለጫዎችን ማስፋፋት አንደኛው ሲሆን፤ በእውነትም ታዲያ በዚህ በኩል ያለውን ግፊትና ያመጣውን ግልጽ ጫና ከትውልዳችንና ዘመኑ ጋር አሰናስለን ስንመለከተው በእጅጉ ተሳክቶላቸው በድሉም ከፍተኛ እርካታንና ድል አድራጊነት የሚያመጣላቸውን ስራ እንደፈጸሙ ማገናዘብ እንችላለን፡፡
+++
እነዚህ የዝሙት ኢንደስትሪዎች ጥፋት አድራሽነታቸውና የትውልድ ልክፍትነታቸው ገሃድ በወጣ እውነታ ያለ ማስረጃና ሰነድ አስፈላጊነት የተረጋገጠ ሲሆን፤ ነገር ግን "ተዉ" የሚላቸው ጠንካራ የመንግሥትና የግለሰቦች ተቋም እምብዛም አለመኖሩን ስናጤን፤ ከዓለም መንግሥታት ጀርባ ያሉት መናፍስታዊ መዋቅር ያላቸው ድርጅቶች ባለ ጠንካራ ሰንሰለታማ አሳሪዎቹ የሚስጢር ማኅበራት ክንድ የቱን ያህል እግዚአብሔር በረሳ ትውልድና ዘመን ላይ በርትቶ እየደቆሰ፣ እየጠመዘዘና እየገፈተረ እንዳለ መረዳት ያስችለናል፡፡ የወሲብ ፊልሞች አደገኝነት በንጽጽር ሲታይ ጥቂት የሚሆኑ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች ጉዳቱንና ሁለ ገብ እከሉን በሰዎች ቋሚ ምስክርነት እያረጋገጡ ትምህርትና መረጃ ቢሰጡበትም፤ የወሲብ ኢንደስትሪዎቹ ከተሰራጩበት ጥልቀትና ስፋት አንፃር፤ እንዲሁ ትውልዱ ውስጥ ሥር ሰደው ካሉት የመናፍስት አገዛዝና አሠራር ምክንያት በቀላሉ ለኃጢአትና ለእርግማን አሳቦችና ድርጊቶች የመሳብ አዝማሚያው ከፍተኛ በመሆኑ፤ እዚህ ግባ የማይባል ለውጥ ሳያመጡ ቀርቶዋል፡፡
✞ የወሲብ ኢንደስትሪና የፋሽን ኢንደስትሪ ጣምራ ሂደት ✞
ከላይ በተገለጸው መልኩ እንደተቀመጠው ጉልህ የሆነና በቁጥርም የበዛ ጥናትና ምርምር ባለመካሄዱ እንጂ በዛሬው ትውልድ እውነታ ውስጥ የዝሙት ኢንደስትሪ ተቋማት የአሻራ ተጽዕኖ ያልነካካው የሕይወት ዘርፍ ፈልጎ ማግኘት የሚያዳግት ይሆናል፡፡ ከነዚህ በታላቅ ተጽዕኖ ውስጥ ውድቀው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚስጢር ማኅበራቱ ተልዕኮና እቅድ ተፈጻሚ ከሆነባቸው የትውልዱ ገጽታዎች መካከል የፋሽን ኢንደስትሪው ይጠቀሳል፡፡
+++
ዛሬ በፋሽን ኢንደስትሪው በኩል በየቀኑ እየተመረቱ የሚወጡት የልብስ ቅርጾችና ይዘቶች፣ የመዋቢያ መሳሪያዎች፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች በአብዛኛው ራቁት ገላን የሚያበረታቱና ዝሙት ነክ እንድምታ የሚነበብባቸው ናቸው፡፡ ርጉማን መናፍስት፤ የዘመኑን ትውልድ የቀልብ አሳብ አዎንታዊ በሚመሰል ስሜት አነሁልሎ በራቁትነት ገጽታ በመሳብ፤ የፋሽንና የአለባበስ ሴሰኝነትን የሚያንጸባርቅ ፍላጎት በመፍጠር፤ በዓይን በመመልከት ብቻ የሕሊናን እምነት መስመር በማሳት፤ ውስጣዊ ዝንባሌን ከመናፍስት ትዕዛዝ በሚመነጭ ግፊት በማስቀልበስ ወሲብ ናፋቂ እንዲኮን ያደርጋሉ፡፡
ዘመናት አስቀድሞ አጭር ቀሚስና ደረት የሚገለብጥ ልብስ መልብስ በተለይ በኛ ማኅበረሰብ እሴትና እይታ መሠረት ነውር የተባለ ሲሆን፤ ዛሬ ነውሩ ረጃጅም ቀሚስ መልበስ እንደሆነ ሁሉ ከተማና ፈረንጅ ቀመስ የኑሮ ዘልማዶቻችን ውስጥ የአእምሮ መፍዘዝን በመናፍስቱ አስገዳጅነት አስቀምጠውብን ራቁትነትን እንደ ባሕል ለውጥ አጸደቅነው፤ 'እሴትን' የዘመን ያለፈ ታሪክ 'ነውርን' የዘመን ነባራዊ እውነት ለማድረግ ተገድደናል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚመረቱትም ልብሶች በብዛት ሆነ ብለው ሙታንታ ላለመሆን ሩብ የቀራቸው ቀሚሶችና አልባሳት ላይ በጣም ያተኮሩ ስለሆኑ፤ ይህንን እንቃወማለን አሊያም አንለብስም የሚሉ ሴቶች እስኪቸገሩ ድረስ ዘመኑ እንደጠቅላላ አጋድሎ ራሱ አስገዳጅ ራሱ ፈራጅ የሆነ ትውልድን ሲያፈራ ከጀርባ ያሉት የመናፍስት ማኅበራት በእጅጉ ረክተውና በግባቸው መሳካትም ተደስተው፤ ዝሙት ዝሙት የሚሸት ኑሮን ከተለያየ አቅጣጫ ለጊዜው ሲያሠለጥኑ እኛ ቢቸገር ነንና ተራ በተራ እስከምንጨነቅ ድረስ፤ ተራ በተራ እስከምንሰቃይ ድረስ ቶሎ አይገባንም፡፡ ቢገባንም ዘመኑንና ትውልዱ እንደሆነው ለመሆን እንጂ የእምነትንና የማኅበረሰብን የእውነት ኃይል ለማስጠበቅ ሰብረን የምናልፍበት እውነቱም፣ ድፍረቱም፣ ፍላጎቱም የለንም፡፡
+++
በመናፍስታዊ ቁራኝነት ተለውሰው የሚለቀቁት የዝሙት ፊልሞችና ምስሎች በብዛት ሴቶችን እንደ ፍትወት ስሜት ማስታገሻ የቆጠሩና ተፈጥሮ ሁነታቸውንም ያከበሩ ስላይደሉ፤ ይህንኑ የመርዝ ዲያቢሎሳዊ ፕሮፖ-ጋንዳ በአልባስና በጌጣጌጥ በኩል እየለወሱት ለትውልዱ ልቦና መጋሸብና መጥፋት መንስኤ ሆነው፤ ሴት ልጆች በአጭር ቀሚስና ቁምጣ፣ ደረት በሚገለብጥ ልብስና ተክለ ሰውነትን በጉልህ በሚያሳይ ፋሽን እንዲያጌጡ የማስገደድ ያህል በስውር እየተጫኑ፤ በዚህኛው በኩል ደግሞ ይመጡና የውበት መለኪያና ደረጃ ራሳቸው ሆነው፤ ያልተራቆተች፣ ዘመኑን ያልመሰለችና ያልተጋጌጠች እንስት ከውበት መለኪያው በታች እንደሆነች፣ በተቃራኒ ጾታ ተመራጭነት ደረጃ ውስጥ ያልተካተተች፣ ኋላ ቀር እንደሆነች፣ ዘመኑን መዋጀት የተሣናትና የኢኮኖሚ ጥገኛ የሆነች እንደሆነች አድርገው በሙዚቃው፣ በፊልሙ፣ በመጽሐፍቱና በመዝናኛ ሚዲያው በኩል ይደሰኩራሉ፡፡
ገንዘብንና የሚዲያ አውታሮችን በመቆጣጠሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና እና ኃይል ያላቸው እነዚህ የዲያቢሎስ እጆች የሆኑት ህቡዕ ድርጅቶች፤ የተራቆተ ልብስና ዘመኑን የሚመስል ልብስ ለመልበስ የሚፈልጉ ቆነጃጅት እንስቶችን እየመረጡ በየፊልምና መዙቃው ኢንደስትሪው የፊት ገጽነትን ሽፋን እየሰጡ፤ የዜናዎችንና የመገናኛ ሚዲያ አትኩሮት አቅጣጫዎችን ቀድመው እየቀየሱ፤ በኢኮኖሚና የዝና ደረጃ እየደገፉ ወደላይ ወደ አርአያነት ደረጃ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ፤ ትውልዱን በነዚህ አርቲስቶችና የሚዲያ ሰዎች በኩል ስቦ መምራት ብዙም የማይቸግር ሆኖላቸዋል፡፡ ካለፉት መቶ ዓመታት ወዲህ በሚያስደነግጥ በከፍተኛ ፍጥነትና ተደራሽነት ወደ ዓለም የተሰራጩት የወሲብ ፊልሞችም የዓለሙን ዘመናዊ ትውልድ የሰብዓዊነት ቅርጽ ከነሥነ ምግባር ገጽታው ከውስጥ በመናፍስት ዳፍንታዊ አገዛዝ ስልት በኩል ስለተቆጣጠሩ፤ በእውነት ያለበሱትን የሚለብስ ትውልድ መገኘቱ ምንም የሚያስገርም አይሆንም፡፡
" ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤"
(የዮሐንስ ራእይ 17፥4)... ይቀጥላል
BY ኰኲሐ ሃይማኖት
Share with your friend now:
tgoop.com/fnoteAemro/263