tgoop.com/fnoteAemro/264
Last Update:
✞ የወሲብ ፊልምና ጠንቆቻቸው ✞
ክፍል - 4
በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን፡፡
✞ የወሲብ ፊልምና የመዝናኛው ኢንደስትሪ ተያያዥነት ✞
በክፍል ሦስት ትምህርታችን ለማንሣት እንደተሞከረው "የወሲብ ፊልሞችና የፋሽን ኢንደስትሪ በጣምራ እንዲጓዙ" የአያያዥነቱን ሚና መሣሪያ ሆኖ የተጫወተው የመዝናኛው ኢንደስትሪው ነው፡፡ አሁን እንዴት ማለት ነው፥ አንድ በሦስት ፈረሶች የሚጎተት ጋሪ ላይ ተቀምጦ የሚንቀሳቀሰን ሰው አስቡ፡ ግለሰቡ ፈረሶቹን ወደሚፈልግበት አቅጣጫ መንገድ በማስያዝ መሪ እየሆነ ወዳሻው ቦታ ይጓዛል፡፡ እንዲሁ ደግሞ ሦስቱን ኢንደስትሪዎች ማለትም የወሲብ ፊልሞችን ኢንደስትሪ፣ የፋሽን ኢንደስትሪ እና የመዝናኛ ኢንደስትሪን በጋራ አያይዞ በመጠቀም የመናፍስት ማኅበራቱ ትውልዱን ወደሚፈልጉበት አኗኗር፣ ሁኔታና የዘመን ገጽታ ለመምራት ችለውበታል፡፡ በዚህ አካሄድ ላይ ዲያቢሎሳዊ ቅኝቶችን እንደ ዓለም ትውልድ በሚገባ አስርጾ ለማስፈን እና የሚፈልጉት የዘመን ትውልድና የሕይወት ዘይቤ እንዲከሰት የሚከተሉትን ስልቶች ተጠቅመዋል፡፡
☞ የሥልጣኔ ዘውጎችን ጤናማ የውስጥ ትርጉማቸውን በማፋለስ፤ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት መነሻ ዓላማ ኪሎ ሜትሮችን ርቆ አፍታ ቆም ብሎ ሳያገናዝብ እንዲጎዝ የዓለም ሩጫዎችን መድረሻ ግብ የሥጋ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት እንደሆነ ብቻ ስለማሳመን ሲሉ፥ በዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ነባራዊ ስዕሎች ውስጥ የሚፈልጉትን አድምቀው በተደጋጋሚ እያሳዩ በመሳብ፤ ተረጋግቶ የዓለም ነገራትን የመፈተሻ ጊዜን እያሳጡ የነፍስ ጥያቄዎችና የሃይማኖት እንድምታዎች የሚጨፈለቁበት ስርዓት መዘርጋት
☞ የሰው ልጆች ሰብአዊ ማንነታቸውን እስኪዘነጉ ድረስ ሌት ተቀን ለሥጋዊ ፍቃዶች ብቻ እንዲሮጡ ዓለምን እንደ ውድድር መድረክ አድርጎ በመቅረጽ፤ መሠረታዊ የእምነት መደንግጎች የሆኑት ፍቅርን፣ እምነትንና ተስፋን በተለያየ ዘዴ በመጉዳት፤ በምትኩ ጉልበት፣ ውበት፣ ገንዘብ፣ ዝና እና ሥልጣን የመኖር መጀመሪያም መጨረሻም ማረፊያ ተልዕኮዎች እንደሆኑ አስመስሎ የሕይወትን ቅርጽ በሥጋዊ አተረጓጎም ውስጥ ብቻ ለክቶ፤ የእምነትንና የባሕልን እሴቶች በየዘመኑ መድምሰስ
☞ የሕሊና፣ የልቦና እና የነፍስ ሰማያዊ ፍቃዶች በተፈጥሮም በሥጋ ስሜቶች የተከለሉ በመሆናቸው፤ እነዚህ መንፈሳዊ ፍቃዶች ወደ ውጪ እንዳይገለጡና ሥጋን እንዳይገዙ ለመቆጣጠር፤ የሥጋ ምቾቶችን የሚያገዝፉ እንዲሁም የሚያስጠብቁ የተብለጨለጩ ስብከቶችን እና ሽልማቶችን ከፊት እያስቀደሙ በማስቀመጥ፤ ፍላጎቶች ሁሉ ተመሳሳይ የሥጋ ዝንባሌ እንዲንጸባረቅባቸው መናፍስታዊ አዚሞችን በመጠቀም የትውልድን የጊዜ መስመር ከመነሻው፣ ከመካከሉ እና ከመድረሻውም ላይ እየሆኑ መቆጣጠር
☞ የሃይማኖትን ኃይልና መንገድ እንደ ጭቆና ቆጥሮ በማስቆጠር፤ የእምነት አካሄዶች የነጻነት ብዝበዛ ተጽዕኖ አሳዳሪዎች እንደሆኑ በተለያዩ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ገለጻዎች ለዓለም በማድረስ፤ ለታሪካዊ ብሎም ለነባራዊ የሕብረተሰብ ችግሮች መንስኤ ናቸው በማለት ተጠያቂነትን ከፈጠሩ በኋላ፤ የሃይማኖት ፋይዳዎችና ጉዞዎችን ማቃለል፣ ማሳደድና ማጥፋት
☞ የፋሽን አልባሳትንና የአካል ተክለ ቁመና ውበትን በፉክክር መልኩ በማቅረብ፤ መገላለጥና መራቆት እንዲሁም የተዛነፈ አለባበስንና ገጽታን መጠቀም እንደ ልዩ የዘመናዊነት መታያ አድርጎ፤ እርቃንን እንደ ትልቅ ጀብዱና ዝና በመቁጠር፤ ለኃጢአት ማደግና ለመቅሰፍት መብዛት ምክንያት መሆኑን ሰው እንዳይረዳ አድርጎ ትውልዱን የፋሽን ምርኮኛ ማድረግ
☞ የማኅበራዊ ድረገጾችን፣ የመገናኛ አውታሮችን፣ የፊልም እና የሙዚቃ ኢንደስትሪዎችን ከሥር ከመሠረቱ በመቆጣጠር፤ በሰዎች ውስጥ ያሉትን መናፍስት ለክፋት አንድነት እንዲተባበሩ የማቀናጂያ ትስስሮሾችን በማመቻቸት፤ ርኩሰት እንዲያይል፣ አመፃ እንዲስፋፋ፣ እርግማን እንዲጸና፣ ሐሰት እንዲበራከት፣ እምነት እንዲሰናከል የማዳከሚያ ዕድሎችን በመጨመር ዘመኑን ከነፍስ ወከፍ አንስቶ በሰይጣናዊ አገዛዝ ሥር መጣል
☞ የሰው ልጆች በአእምሮ አመዛዛኝነትና በሕሊና ፍረደኛነት ነገሮችን እንዳያስተውሉ ስሜታዊነትን እንደ ደስታ መሸመቻ እንዲሁም ማንጸባረቂያነት በማድረግ፤ አስፈላጊ የኑሮ ግንኙነቶችንና ግንባታዎችን በአጥፊ መናፍስት መሪነት ሥር የወደቁ አጋጣሚ የሚመስሉ ሁነቶች ላይ እንዲጀምራቸው የተለያዩ የፌዝ፣ የቲዎሪና የፍልስፍና ጽንሰ ሐሳቦችን በመዝናኛ ማዕከላት በኩል በገፍ በማሰራጨት፤ አጢኖ የማስተዋልንና የሚመጣውን አሻግሮ የመመርመርን መንፈሳዊ ኃይል በማድከም፤ ስለቅርብ ቅርቡ ክስተቶች ብቻ እንዲኖሩ በውጪያዊ ግፊት ውስጥን ማጨለም
+++
ዓለምን በአንድ ማዕከላዊነት ለመጠቅለል ከሚያገለግሉ ታላላቅ መሣሪያዎች መካከል አንደኛው የሆነው የመዝናኛው ኢንደስትሪ፥ በተለይም ዛሬ ዛሬ ተጽዕኖው እጅግ ሥር የሰደደና የአጥፊዎቹን የርኩሰት ኃይሎች ለጥፋት የሚውልን ድካም ያቀለለ፤ በአያያዥ ሰፊ አድማስነቱ በኩልም ብዙ የኃጢአት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ መንገድ የሆነ ተቋም መሆንን ችሏል፡፡
በዛሬይቱ ዘመን ላይ ደግሞ የመዝናኛ ኢንደስትሪዎች ጫናና ስርጭት በብዙ የአኗኗር አቅጣጫዎች ላይ ተገኝቶ የአሁኑን ትውልድ ጉዞ መሪ መሆን የቻለ፤ በአቋሙ ግንባታ ውስጥም ሰርጎ ገብቶ ወደ ውጪያዊ ገጽታ ሊያውም እንደሚያኮራ ሆኖ እየተገለጠ ያለ፤ በቋንቋና ማንነት ላይም የራሱን አሻራ ያለ ብዙ አድካሚ ውጣ ውረድ ማኖር የቻለ በመሆኑ፤ ይህንን ተከትሎ የዘመኑ ወጣቶች ኑሮና ሕይወት ምን መልክ ያዘ ስንል የሚከተሉትን እናገኛለን፡፡
❖ በሚታየው የመዝናኛ ኢንደስትሪ ውስጥ ባሉት የፊት ገጽ አርቲስቶችና ፊት አውራሪዎች አማካኝነት የሚሰጠውን የንግግር፣ የአለባበስና የአኗኗር ልማዶችን ሳይጨምር ሳይቀንስ ወደራሱ ማንነት ያንጸባረቀ ሲሆን ታዲያ፤ አሁን አርቲስቶቹ ሲንጨባረሩ ትውልዳችንም ይንጨባረራል፣ ጠምዛዦቹ ሲራቁቱ ትውልዳችንም ይራቆታል፣ ፊት አውራሪዎቹ ሰላምታቸው ስድብ አዘል ሲሆን እዚህም እኛም ጋር ጸያፍ ቃላት "ደህና አደርክ?"ን ተክተዋል፡፡
❖ አብዛኛዎቹ በመዝናኛው ማዕከላት የሚንጸባረቁት የታይታ ገጽታዎች ሥጋዊ ምቾቶችን የሚያሳዩና ነጻነት መሰል መረን የለቀቁ አንዳንዴም ግልጽ እብደቶችን የሚወክሉ ናቸውና፤ ትውልዳችንም ይህንን የሥጋ ምቾት ለመቀዳጀትና በእንጀራ ብቻ የተመሠረተ ኑሮን ለመገንባት ሲል እርስ በእርሱ በዘመናዊነት ልኬት የሚወዳደር፣ በኢኮኖሚ ደረጃዎች ለመበላለጥ የሚውተረተር፣ ከፊት ፊት ቀድሞ ለመታየት በሚደረገው ጥረት ውስጥ እርስ በእርሱ ከውስጥ የተገፋፋ፤ አንድነትና መተባበር የራቀው ዜጋ ሆነና ቁጭ አለ፡፡
❖ በተጨማሪ ሃይማኖታዊ እውነታዎችን፣ አገረሰባዊ ባሕሎችንና ቤተሰባዊ መስተጋብሮችን የሚንቅ፤ በሥልጡንነት ጓዳና ላይ ለመጓዝ የእምነት ጫናዎችን እንደ ጎታች ተጽዕኖ የሚቆጥር፤ ወደፊት መሄድ ማለት የኋላውን መናድና በእርሱ ቦታ አዲሱን ተክቶ መራመድ የሚመስለው፤ ነገራትን ሁሉ ከሥጋ ፍቃድና ዓይን ብቻ የሚለካ፥ ግራ ግብት ያለው፥ መንፈሳዊ ሞገሱን የማያውቅ፣ ጸጋና ራእዩን ያጣ፣ የአባቶቹን የታሪክ ፈለግ ማግኘት የተሣነው፣ ለውሳኔ የሚቸገርና ሁልጊዜ የድካም ስሜት ያልተለየው ትውልድ ሆነን፤ እንዳደረጉን የምንሆን መሞከሪያ አሻንጉሊቶች በመሆን ሰማያዊ ኃይል ርቆን እንባትታለን፡፡ ይቀጥላል....
BY ኰኲሐ ሃይማኖት
Share with your friend now:
tgoop.com/fnoteAemro/264