tgoop.com/maheteben123/20377
Last Update:
«ዝክረ ኒቅያ» ሀገር አቀፍ የሊቃውንት ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው !
የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም
<<የሊቃውንት ብዛት ለዓለም መድኃኒት ነው>>
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ታሪካዊና በዓይነቱ ልዩ የሆነ <<ዝክረ ኒቂያ>> የተሰኘ ሀገር አቀፍ የሊቃውንት የምክክር ጉባኤ ከሚያዚያ 20 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ለማካሔድ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ የጉባኤውን ዓላማ እና ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሕዝብ ግኑኝነት ጽ/ቤት መግለጫ በሊቃውንት ጉባኤ ተሰጥቷል፡፡
በቀደምት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥያቄዎችና የኑፋቄ ትምህርቶች ሲነሱ መልስ ለመስጠት ሊቃውንቱ ተሰባስበው ምላሽ የሚሰጡ መሆኑንና አሁንም በቤተ ክርስቲያን ላይ በነገረ ሃይማኖት እንዲሁም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተለያዩ ኑፋቄና ቀኖናዊ ጥያቄዎች እየተነሱ በመሆኑ የሊቃውንት መሰባሰብ አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ጉባኤው ከጥር 26-29 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለማካሄድ ታቅዶ እንቅስቃሴ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም፡-
1ኛ) ጉባኤው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የጉባኤ ቤት መምህራንና ሊቃውንት የሚታደሙበት እንደመሆኑ፥ በተለይ በጠረፉ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ መምህራንን በበቂ ቊጥር ለማካተት እንዲቻል ፥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተጨማሪ ጊዜ በማስፈለጉ ፤
2ኛ) በጥር ወር በርካታ ሀገራዊ ክንውኖችና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት በየአካባቢው የሚካሄዱ በመሆናቸው የጉባኤው መካሄጃ ጊዜ እንዲስተካከል ከአንዳንድ አህጉረ ስብከት በተደጋጋሚ አስተያየት በመሰጠቱ ፤
3ኛ) ጉባኤው ከዘመናት ቆይታ በኋላ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድና በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ውይይቶችን በማካሄድ ፥ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚጠቅም የውሳኔ ሐሳብና አስተያየት የሚያቀርብ ፥ አልፎም የአቋም መግለጫ የሚያወጣ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፥ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፥ የጉባኤ ቤት መምህራንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፥ የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በሚገኙበት ከሚያዝያ 20-25 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚካሄድ ይሆናል።
በጉባኤው፡- ያለውን ማጽናት፣ የጠመመውን ማቅናት፣ የጠፋውን መፈለግ፣ ሊቃውንቱን እርስ በእርስ ማስተዋወቅና ቤተክርስቲያን ያለችበትን ችግር ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ እና ብፁዓን አበው በተገኙበት ለምልአተ ጉባኤው ጥያቄ የሚቀርብ እና ምላሽ እንዲሰጥበት እንደሚደረግ ግቡን ማድረጉ ተገልጧል፡፡
ከመላው የሀገሪቱ ክፍል ከተቻለም ከውጭው ዓለም ያሉ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የሚሰባሰቡ ሲሆን በጊዜው በኒቂያ እንደተደረገው በዚህ ጉባኤም 318 ሊቃውንት የሚታደሙ እንደሆነ በመግለጫው ተገልጧል፡፡
በብፁዕ አቡነ እንድርያስ ሰብሳስቢነት የሚመራው የሊቃውንት ጉባኤ ከ 15 በላይ አባላት ያለው መሆኑ በመግለጫው ላይ ለማስታወስ ተሞክሯል፡፡
BY ማህተቤን አልበጥስም የተዋህዶ ድምፅ ✝💒
Share with your friend now:
tgoop.com/maheteben123/20377