tgoop.com/manbabemuluyadergal/1954
Last Update:
የማይካዱ እውነታዎች
ምኒልክ ስምህን - ከአድዋ ነጥዬ፣
እንዴት አከብራለሁ - ድሉን የእኔ ብዬ?
አንተ ብትኖር ነው - አንተ ብትመራው፣
የአንድነት ኃይላችን - የድል ፍሬ ያፈራው።
........
ምኒልክ ተጽፏል - በማይጠፋ ቀለም፣
አድዋን የሚውጥ - የጥቁር ታሪክ የለም።
........
የሠራኸው ሥራ - ገዝፎ ሲታያቸው፣
እንዳንተ እምዬ - መባል ሲያቅታቸው።
ከመሬት ከፍ ብለው - ምንም ሳይታዩ፣
ስምህን በማጥፋት - መስሏቸው ሚቆዩ።
የአንተን ፎቶ አንስተው - የእነሱን በማድረግ፣
ታሪክ አይፍቀውም - የምንሊክን ማዕረግ።
.........
ጊዜ ያነሳው ሰው - ትናንትን አስታውሶ፣
ቢቀጣ በዳዩን - ልቡ ቂምን ለብሶ።
መሆኑን ያሳያል - የሌለው ችሎታ፣
መያዝ ማይገባው - ከፍ ያለውን ቦታ።
............
ባለው አቅም ጠንክሮ - ሠርቶ እንደማሳየት፣
ሰነፍ ከጎበዝ ጋር - አይችልም መቆየት።
ሁልጊዜ ሰነፍ ሰው - ለራሱ ሲፈራ፣
ይጥራል ሊደብቅ - የጎበዙን ሥራ።
.........
ጎበዝ ሰው ምንጊዜም - ሠርቶ እያሳየ፣
በችሎታው ልቆ - ሆኖ የተለየ።
ሀገርና ስሙን - ከፍ አድርጎ ያስጠራል፣
ሰነፍ ግን ሁልጊዜ - በማፍረስ ይቀብራል።
..........
ከታች ሆነው አልቅሰው - ከላይ ሆነው አልቅሰው፣
መኖር ከሚያምራቸው - ያለፈውን ወቅሰው።
ለምን ያላቸውን - ችሎታ በማውጣት፣
ተሽለው አይገኙም - ሰላምን በማምጣት?
..........
የያዘውን ትቶ - ህፃን ሌላ ያነሳል፣
የእኔ ነው እያለ - በሰው ዕቃ ያለቅሳል።
አዋቂ ሰው አየን - በቂ ማዕረግ ይዞ፣
ጀግና በሉኝ የሚል - ታሪክ አደብዝዞ።
..........
ሰውን አታታልል - በሰው ዝና አትቅና፣
ያልሆንከውን ሆነህ - አትጠብቅ እውቅና።
እንደ እምዬ ደምቀህ - ከፍ ብለህ እንድትታይ፣
ጀግና ነኝ የምትል - ጀግና ሆነህ አሳይ።
..........
መክብብ
February 28, 2023
BY የመፅሐፍ አለም 🇪🇹🇹
Share with your friend now:
tgoop.com/manbabemuluyadergal/1954