tgoop.com/medrekenean/392
Last Update:
ከፕሮቴስታንት-ተሐድሶ መናፍ**ቃ*ን ጋር ስንነጋገር ገድላትን ለኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መከራከሪያ አድርገን አናቅርብ፣ በሐዋርያውያን ትውፊታውያን አብያተ ክርስቲያናት ከጥንት ጀምሮ የመጣውን አስተምህሮ አብራርተን ማቅረብ የምንችልበትን ጊዜ በአግባቡ እንጠቀም ማለት ገድላት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እና መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ ለመረዳት አያስፈልጉንም ማለት አይደለም። ነገር ግን ለመወዛገብ በር የማይከፍቱ በግእዝ ብቻ ሳይሆን በግሪክ፣ በላቲን፣ በእብራይስጥ ጭምር የተመሳከረ ቅጅ (edition) ያላቸው ጥንታውያን ድርሳናትን ጠቅሰን ሐዋርያዊውን ኦርቶዶክሳዊ እምነት ማሳየት በምንችልበት ሁኔታ ለምን እነርሱ በመረጡት ሜዳ ላይ እንከራከራለን ለማለት ነው። ስለ ገድላት ብዙ ማጥናት እና የታረሙ ቅጅዎችን ማዘጋጀቱ በጣም አስፈላጊ ሥራ ነው። በጥልቀት ብንመረምራቸው እጅግ ጥልቅ ትምህርቶች እንዳሉዋቸው ይታወቃል። ብዙ ረቂቅ (mystical) መለኮታዊ ሐሳቦችን ይዘዋል። ነገር ግን ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ ለማስረዳት በገድላት ላይ መመሥረትና ዋናውን ጉዳይ እዛ ላይ ያሉ ጉዳዮችን ለማብራራት ማዋል የአካሄድ ስሕተት (methodological fault) ይመስለኛል። በጊዜ ቅደም ተከተልም ስናየው ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ከአብዛኞቹ ገድላት ይቀድማል፤ ገድላት በዚያ አስተምህሮ አምነው የኖሩ ቅዱሳን ተጋድሎን የሚያሳዩ ናቸውና። በመሆኑም በ4ኛው መ/ክ/ዘመን በሁሉም ዓለም ተንሰራፍቶ የሚገኝን ትምህርት ትክክለኝነት ለማስረዳት በ14ኛው መ/ክ/ዘመን የተጻፈ የአንድ ቅዱስ አባትን ገድል ዋና መከራከሪያ አድርጎ ማቅረብ ጊዜን መገልበጥ (anachronism) ይሆናል።
ስለገድላት እና ተአምራት በራሳቸው ርእስ አድርጎ መነጋገርም መከራከርም ችግር የለውም። እነ ወንድም ዘማርያም ገድላትን እንዴት መመልከት እንዳለብን ያሳዩበት መንገድ መልካም ነው። የበለጠ ደግሞ የተለያዩ ቅጅዎች ተጠንተው መታረም የሚያስፈልጋቸውም አሉ። ዋናውን ነገረ-ሃይማኖታዊ ጉዳይ ለመሸፈን ክርክሩን ሁሉ ገድላት እና ተአምራት ላይ ለማድረግ የሚፈልጉ አካላት ስላሉ ያነን መፍቀድ የሚገባ አይመስለኝም።
አጠንክሬ መናገር የምፈልገው ከ*መና*ፍቃ*ን ጋር በሚደረጉ ክርክሮች ዋናውን ጉዳይ ገድላትን ተአምራትን ወደማብራራት አናድርገው ማለት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ዝቅ አድርገን እንይ ለማለት አይደለም፤ ሌሎች በዓላማ ስለሚጠቀሙባቸው እና ብዙዎቹ የተጣራና የተመሳከረ ቅጅ (edition) ስላልተሰራላቸው ጉዳዩ ከጥንት ጀምሮ ወደሚታወቁ ድርሳናት ቢወሰድ ይሻላል ለማለት እንጂ።
Bereket Azemeraw
👉 @tonetore
BY ከነዓን ሚዲያ - Kenean Media
Share with your friend now:
tgoop.com/medrekenean/392