tgoop.com/ortodoxtewahedo/26055
Last Update:
✝️7ቱ ኪዳናት✝️
ሰባቱ ኪዳናት "ተካየደ" ማለት "ተስማማ : ተማማለ" እንደ ማለት ሲሆን "ኪዳን" በቁሙ "ውል : ስምምነት" እንደ ማለት ነው:: ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር: ሰዎችም ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል:: ልዩነቱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው:: እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጓል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ 7 እንደ ሆኑ ታስተምራለች:: :: "ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ" "ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ" (መዝ. 88:3)
#1 ኪዳነ አዳም አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት: የፍጡራን አስተዳዳሪ: ነቢይ: ካህንና ንጉሥ ነው:: እግዚአብሔር ከአዳም ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው:: ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ:: (ዘፍ. 3:1) አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን ተስፋ: "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ኪዳንን ተቀበሉ:: (ቀሌምንጦስ: ገላ. 4:4)
#2ኪዳነ ኖኅ ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት 10 ትውልድ ዓለም በዓመፃ ተሞላች:: ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች:: ከመርከቡ ከወጣ በኋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ተጋቡ:: "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ" እንዲል:: (ዘፍ. 9:12)
#3 ኪዳነ መልከ ጼዴቅ መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ: የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው:: በ15 ዓመቱ መንኖ: አጽመ አዳምን ይዞ: በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት ነበር:: እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ: በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል:: በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም:: ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል:: (ዘፍ. 14:17, ዕብ. 7:1)
#4 ኪዳነ አብርሃም ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት: ሥርወ ሃይማኖት: የጽድቅም አበጋዝ ነው:: ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና እግዚአብሔር "በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ" አለው:: (ዘፍ. 12:1) የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን ሰጠው:: (ዘፍ. 17:1-14)
#5 ኪዳነ ሙሴ ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ: የእሥራኤል እረኛ: የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው:: በፈጣሪው ትዕዛዝ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለ40 ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል:: (ዘጸ. 20:1, 31:18)
#6 ኪዳነ ዳዊት ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት: ጻድቅ: የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው:: እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ" (መዝ. 131:11) ሲል ምሎለታል:: አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ "አልዋሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን:: (መዝ. 88:35)
#7 ኪዳነ ምሕረት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ስድስቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲዖል ማዳን ግን አልቻሉም:: ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ ነበር:: ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ:: በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ: አድጎ: ተጠምቆ: አስተምሮ ለአለም ቤዛ የሆነበት ነው ።
@ortodoxtewahedo
BY ኦርቶዶክስ ተዋህዶን እንወቅ
Share with your friend now:
tgoop.com/ortodoxtewahedo/26055