tgoop.com/sofimemo/377
Last Update:
"ተከራያችን"
ክፍል ፫
ደራሲ ፦ ሶፊ
የጀመርኩትን ስራ ዳር እንኳ ሳላደርስ ማልጄ ተነስቼ ጉዞዬን ወደ ቤት መጓዝ ጀመርኩ...
ረዘም ያለ ጉዞ ስለሆነ እንደቀደመ ጊዜዬ እንደማደርገው በመስኮት በኩል ተቀምጬ ቀና ስል የተፈጥሮን ውበት እየተመሰጥኩ...ጎንበስ ስል ስለህይወት የሚያወጋውን የበዓሉ ግርማን "ደራሲው" የተሰኘውን መፅሐፍ እያጣጣምኩ መንገዱን ባማረ ሁኔታ ተጓዝኩ...ብቻ ጭንቅላቴ ምን ሆና ይሆን? ምንድነው ያመማት እያለ በመሀልበጥያቄ ያጣድፈኛል ሀሳቡን መልስ ስለማላገኝለት ችላ እለዋለሁ...አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ ገባኹ...ብዙም እቃ ስላልያዝኩ ጠደፍ ብዬ ታክሲ ያዝኩ...ቅርብ የነበረው ቤት ራቀብኝ የማያልቅ መንገድ ማብቂያ የሌለው ጉዞ መሰለኝ...ቤት ደርሼ የምትወደኝን እስካይ ጓጉቻለሁ። የጥያቄ መሀት ድንገተኛ አደጋ አጋጥሟት ይሆን ? እማዬ ደግሞ እንደዛ አላለችኝም። እሺ ምን ሆና ነው ? ምንድነው መድረስ ሲፈልጉ መንገዱ የሚርቀው እያልኩ ስነጫነጭ ሰፈር ደረስን።
የሰፈር ሰዎችን ሰላም ነው? እግዚአብሔር ይመስገን እያልኩ ለሰላምታ እዳያቆሙኝ ጎንበስ እያልኩ እጅ እየነሳው ወደ ቤት ተንደረደርኩ...የጊቢ በር ቁልፍ ስላለኝ ሰተት ብዬ ገባሁና ቅድሚያ ወደ ተከራያችን፥የምትወደኝ ወደ እርሷ ቤት ምንም ሳላንኳኳ ገባኹ(ከዛ ቀደም አንድም ቀን ቤቷ ገብቼ አላውቅም እንዲሁ እልፍ ስል አየዋለሁ እንጂ)...ጋቢ ለብሳ ሶፋው ላይ ጋደም ብላ ስልኳን እየነካካች ነበር...ድንግጥ አለች...እኔ መሆኔን ስታውቅ ስልኳን ወርውራ ለመነሳት ስትል እዛው ሁኚ አኳትና ሄጄ አቀፍኳት...ዘለግ ላለ ጊዜ ጥብቅ አድርጌ አቀፍኳት ግን አልታወቀኝም...አንገቷን ወደኋላ ሳብ አድርጋ ጉንጬን ሳም አደረገችኝና "ይበቃል ልትገለኝ ነው እንዴ?" ለምን እንደሆነ አላውቅም የማጣት ድጋሚ አይኗን የማየው አልመሰለኝም ነበር።ግንባሯን ሳም አድርጌ በርከክ ካልኩበት ተነስቼ...የጥያቄ ናዳ ማግተልተል ጀመርኩ
"ደህና ነሽ? ምን ሆነሽ ነው ? ምንሽን ነው ያመመሽ? እንደሚያምሽ ነግረሽኝ እኮ አታውቂም ድንገት ምን ተፈጥሮ ነው ሆስፒታል ለሶስት ቀን የገባሽው? ፊትሽ ልክ አይደለም ገርጥተሻል? ቆይ እሺ ምንድነው አሉሽ ዶክተሮቹ?"ቀን ሙሉ ጭንቅላቴ ሲጨቀጭቀኝ የነበረውን ጥያቄ ዘረገፍኩት።
ከት ብላ ሳቀችብኝ ኧረ በስመአብ ምንድነው ይሄ ሁሉ ጥያቄ ፤ ትንፋሽ ውሰድ እንጂ። ደግሞ ዛሬ ስለህመሜ ምንም ላወራህ አልፈልግም አንተም ከመንገድ ነው የመጣኧው እናትህም ደጅ ደጅ ሲያዩ ነበር ሂድ ሰላም በላቸው ናፍቀዋል።
አሁን ግን እንዴት ነሽ እሺ ? አልኳት አይን አይኗን እያየሁ። አሁንማ በደንብ አገገምኩ ተመስገን እድሜ ለእናትህ አጥሚቱ ምግቡን በላይ በላይ ሲልኩልኝ ነበር። ጥያቄ ባለመመለሱ ቅር እያለኝ "ሰላም ከሆንሽ መልካም ልክ ነሽ አንቺም አረፍ በይ በጥያቄ አላድርቅሽ በቃ ነገ ውጪ እንገናኛለን ሰላም እደሪ።" ግንባሯን ሳም አድርጌያት ወጣኹ።
ቅድሚያ እናቴን ገብቼ ባለማየቴ ራሴን ታዘብኩት..."እማ እናቴ" እያልኩ ሳሎን ስገባ ጭር ብሏል...ልጅቷ ብቻ ነው ያለችው ሰላምታ ከሰጠዋት በኋላ እማዬስ ስላት መኝታ ቤት እንደሆነች አሳወቀችኝ...ከፍቴ ስገባ እናቴ ፀሎት እያደረሰች ነበር...ዞር ብላ ፈገግ አለችና ወደ አልጋው ቁጭ እንድል ጠቆመቺኝ ምንም ሳልናገር ሄጄ ጋደም አልኩ እና ፀሎት እስክትጨርስ ጣራ ጣራውን እያየው ተጠባበኳት...ፀሎቷን ስትጨርስ ሶፊ ወርቅ መጣኧልኝ አለችና ግንባሬን ሳም አድርጋ አቀፈቺኝ
ዛሬ እንደምትመጣ ለምን አልነገርከኝም...ብላ የፀሎት መፅሐፉን አሳለመችኝ...እኔም እንደምመጣ አላወኩም ነበር አልኳት አይኔን ከአይኗ እያሸሸው፤ ስዋሽ አይኔን መርምራ የምታውቅብኝ ይመስለኛል...የሄድክበት ስራ ተሳካ አለችኝ አዎ ተሳክቷል አልኳት...ደአይነት ልጅቷ ቡና እንድታቀራርብ ንገራት እንኳን መጣህ ቤቱ ጭር ብሏል አለችኝ...መጠጣት ባልፈልግም እሺ አልኳት።
ራት በልተን ቡና ጠጥተን...የተለመደው አይነት የእማዬን ደስ የሚል ጨዋታ ከድሮ ታሪክ ጋር እያነሳች ስታወጋኝ ቆይተን ወደ መኝታ ሄድን።ደክሞኝ ስለነበር ወዲያው ነው እንቅልፍ የወሰደኝ።
ጠዋት ማልጄ ተነሳው...የምትወደኝ ጋር ደወልኩ እና በሩን እንድትከፍትልኝ ነገርኳት...ተነሳሁና ቀስ ብዬ እነእማዬን እንዳልቀሰቅስ እየተጠነከኩ ወደ ቤቷ ሄድኩ ገርበብ አድርጋው ትታው ተመልሳ ሄዳ ተኝታለች...ሁለታችንም አንድ ነን የጠዋት እንቅልፍ አይሆንልንም።ገብቼ ወደ አልጋዋ በርከክ ብዬ በጎ ማደሯን ጠይቄያት...ረፋዱ ላይ ልንገናኝ ቀጠሮ ያዝን እና ተሰናብቻት ወጣሁ።
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ደረሰች ሳነብ የነበረውን መፅሐፍ ከድኜ ሰዓቱን ተመለከትኩ ከተቃጠርንበት 10 ደቂቃ ቀድማለች...እንደወትሮ መጠጥ ቤት አልተቀጣጠርንም...ካፌ ነበር የተገናኘነው።ረዘም ያለ ጥቁር ኮት፣ጅንስ፣ሱሪ፣ቡትስ ጫማ፣የፀሐይ መነፅር...ህመሟ ውበቷል ሊጋርደው ሊደብቀው አተቻለውም።
ቁሜ ለሰላምታ ጠበኳት ፈጠን ብላ መጥታ ተጠመጠመችብኝ...ለተመለከተን እረጅም ጊዜ ያልተያየን ጥንዶች እንመስላለን።
ወንበር ስቤ እንድትቀመጥ ጋበዝኳት...ፈገግ ብላ "ሶፊዬ እንዳንተ የሚንከባከብ ወንዶችን ያብዛልን" አለች። "ማለት ብዙ ወንዶች እንዲከቡሽ ነው የምትፈልጊው? "አልኩ ቅናት ቢጤ እየሸነቆጠኝ።
አስተናጋጁን ማኪያቶ እና ኬክ አዘዘችው፤ወደ እኔ ዞራ "ኬክ እንዴት እንደናፈቀኝ" ብታውቅ አለቺኝ።በመገረም "ኬክ እኮ ጣፋጭ ነው...ማኪያቶም ስኳር..." "አቋረጠችኝና እና እኔ ጣፋጭ አይወድልኝም ያለህ ማነው?" "አይ ከእኔ ጋር ሁሌ..." "ሶፊ እኔ እና አንተ እኮ ሲመሽ ነው የምንገናኘው ማታ ማታ ደግሞ መጠጣት ነው የምፈልገው!"አለችኝ ረገጥ አድርጋ።
ተረጋግታ ተቀመጠች እንደቀደመ ጊዜ መቅበጥበጥ አላየሁባትም።
"ከማን ነው የምትሸሽው?" አልኳት።ጥያቄዬ ድንገት ስለነበር እንደመደንገጥ አለችና "ኸረ ከማንም።" አለች "ሰው ብዙ ጊዜ አዘውትሮ የሚጠጣው የሆነ የሚሸሸው እውነት ሲኖር ነው።ከራስሽ ጋር ግን አውርተሽ ታውቂያለሽ ማለት ሁሌም ሽሽት ላይ ያለሽ ነው የምትመስይው።ቀን በስራ ስትዳክሪ ታመሻለሽ...ማታ ዳንኪራ ቤት ነሽ።" ምንድነው የሆንሽው ?"
"አላውቅም ብቻ ግን እንዲህ አልነበርኩም" ብላ ዝም አለች።
እሺ እሱን ሌላ ጊዜ ማውራት ስትፈልጊ ትነግሪኛለሽ...አሁን ምንድነው ድንገት ያመመሽ?
ትክዝ ብላ "ድንገት አይደለም...ሁሌ ልነግርህ እያልኩ ትጨነቃለህ ብዬ የምተወው...እኔም ህመሜን ካወኩ 1 አመት ሆነኝ ብቻ አሁን ብሷል ስላሉኝ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለሆነ ነው ልነግርህ የወሰንኩት"አለች እንዳቀረቀረች። በጣም ደነገጥኩ አመዴ ቡን አለ።አስተናጋጁ ያዘዘችሁን ከፊቷ አስቀምጦ ሄደ።
እሺ ምንድነው ? ንገሪኛ አልኩ።
"ሶፊ እዚህ ምድር ላይ ለትንሽ ጊዜ የመጣው እንግዳ ነኝ።" አለች ቀና ስትል እያለቀሰች መሆኑን አስተዋልኩ...ሶፍት አንስቼ እየሰጠዋት...ይሄ ምን ማለት ነው ?ምንድነው የምታወሪው ሁላችንም እንግዳ አይደለን አልኳት በድንጋጤ እየተርበተበትኩ።"ስምንት ወራት ብቻ ነው ያለሽ አሉኝ" አለችና ሲቃ በተቀላቀለበት ድምፀት ማልቀስ ጀመረች።እንባ ቢተናነቀኝም አብሪያት አላለቀስኩም።እንደምንም አቅፌ አባበልኳት ከዝምታ በቀር ግን የማፅናኛ ቃል አላገኘውላትም።
ይቀጥል?
👉👂🤗 @bestletters
BY Sofi's memo
Share with your friend now:
tgoop.com/sofimemo/377