tgoop.com/tikvahethiopia/70974
Last Update:
ተፈትኖ የወደቀው ፌስቡክ ❌
ፌስቡክ ፤ በኢትዮጵያ ሶስት ብሔሮች ላይ ያነጣጠሩ #የጥላቻ_ንግግሮች ያዘሉ ማስታወቂያዎች ይለይ እንደሆነ የተሰጠውን ፈተና መውደቁ ተሰምቷል።
ፌስቡክን የሙከራ ማስታወቂያዎችን በመጠቀም የፈተኑት " ግሎባል ዊትነስ " እና " ፎክስ ግሎቭ " የተባሉ ሁለት ተቋማት ከቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ዳግም አፈወርቅ ጋር በመተባበር ነው።
ምርመራው የተከናወነው የፌስቡክ የጥላቻ ንግግር መለያ ምን ያህል ጥሩ እንደሆነ ለመፈተን እና የኩባንያው የደህንነት መቆጣጠሪያ ስልቶች ሁከት የሚያባብሱ ማስታወቂያዎችን መከላከል ይችል እንደሁ ለመፈተሽ ነበር።
በአማርኛ ቋንቋ በፌስቡክ የተጻፉ 12 የከፉ የጥላቻ ንግግሮችን የለዩት ምርመራ አድራጊዎቹ እነዚሁኑ ይዘቶች ለኩባንያው እንደ ማስታወቂያ በማቅረብ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ለመለጠፍ ይፈቅድላቸው እንደሁ ሙከራ አድርገዋል።
የኩባንያውን የቁጥጥር አቅም ለመፈተሽ በምሳሌነት የተመረጡት የጥላቻ ንግግሮች የተካተቱባቸው ማስታወቂያዎች፤ የአማራ፣ የትግራይ እና የኦሮሞ ብሔሮች ላይ እኩል ያነጣጠሩ ናቸው።
በማስታወቂያዎቹ አረፍተ ነገሮች መካከል " ሰዎች እንዲገደሉ፣ እንዲራቡ ወይም ከአንድ አካባቢ እንዲጠፉ በቀጥታ ጥሪ የሚያደርጉ፤ ሰዎችን ከእንስሳት ጋር የሚያነጻጽሩ እና ሰብዓዊነት የጎደላቸው” ገለጻዎች እንዳሉበት ተገልጿል።
አብዛኞቹ የማስታወቂያዎቹ ይዘቶች የዘር ማጥፋት እንዲፈጸም ጥሪ የሚያቀርቡ መሆናቸውም ተገልጿል። ከእነርሱ ውስጥ አንዳቸውም ለመተርጎም ውስብስብ እንዳልነበሩ ተመላክቷል።
ግሎባል ዊትነስ ፤ " የትኞቹንም ማስታወቂያዎች አላተምናቸውም። የሚታተሙበትን ቀን ወደ ፊት እንዲሆን በማድረግ፤ ፌስቡክ ማስታወቂያዎቹን መቀበል እና አለመቀበሉን ካሳወቀን በኋላ አጥፍተናቸዋል " ብሏል።
የጥላቻ ንግግሮቹ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ለህዝብ ይፋ አለመደረጋቸውን አረጋግጧል።
በምርመራው መሰረት ፌስቡክ የቀረበሉትን 12ቱንም የጥላቻ ንግግሮች በማስታወቂያ መልክ በገጹ እንዲቀርቡ ፈቃድ ሰጥቷል።
ሁሉም ማስታወቂያዎች ፌስቡክ በአጠቃቀም መመሪያው (community standards) የጥላቻ ንግግር ብሎ ከሚበይናቸው ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።
በሙከራ ደረጃ ፌስቡክ የተፈተነባቸው ማስታወቂያዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ላይ ለዕይታ ቢበቁ ኖሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከ57 አመታት በፊት የጸደቀውን ስምምነት የሚጥሱ ነበሩ።
ስምምነቱ ማናቸውም አይነት የዘር መድሎዎ ለማስወገድ የጸደቀ ነው።
በድርጅቶቹ ምርመራ የተገኘው ውጤት በስተመጨረሻ የቀረበለት ፌስ ቡክ፤ ማስታወቂያዎቹ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው እንዲታተሙ መፈቀድ እንዳልነበረበት ማመኑን ግሎባል ዊትነስ አሳውቋል።
ፌስቡክ ለኢትዮጵያ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የደህንነት ቁጥጥሩን ለማጥበቅ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን መግለጹንም ምርመራውን ካከናወኑት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ግሎባል ዊትነስ አመልክቷል።
Credit - www.ethiopiainsider.com
@tikvahethiopia
BY TIKVAH-ETHIOPIA
Share with your friend now:
tgoop.com/tikvahethiopia/70974