tgoop.com/yeabewu/19
Last Update:
"ሁሉን የያዘውን ያዙት፤ ሁሉን የሚገዛውን አሠሩት፤ የህያውን አምላክ ልጅ አሠሩት፤ በቁጣ ጎተቱት፤ በፍቅር ተከተላቸው። በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተለ ወሰዱት፤ ሊቃነ መላእክት በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤
ኃጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፥ በመኳንንት የሚፈርደውንም በእርሱ ፈረዱበት፤ ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የሾህ ዘውድ አቀዳጁት፤ ለኪሩቤል የገርማ ልብስ የሚያለብሳቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት፤ ኪሩቤል በእሳት ክንፍ ተሸፍነው በፊቱ የሚሰወሩለትን እርሱን ክፉ ባሪያ አሥሮ ፊቱን ጸፋው፤ የመላእክት ሠራዊት በፍጹም መደንገጥ የሚሰግዱለት እየዘበቱበት በፊቱ ተንበረከኩ፡፡
ይህን ያህል ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው? ይህን ያህል ትእግስት እንደምን ያለ ትእግስት ነው? ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው? ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው? ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው በደል የሌለበትን እንደበደለኛ ሰቀሉት፡፡ ህይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ቆጠሩት፤ አዳምን የሠሩ እጆች በመስቀል ቀኖዎት ተቸነከሩ፤ ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ተቸነከሩ፡፡
ወዮ በአዳም ፊት የህይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ ከሃሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መፃፃን ጠጣ፤... ወዮ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምንስ አንደበት ነው? የፍቁሩ የጌታ ህማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል፤ ህሊናም ይመታል፤ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች፤ ሥጋም ይደክማል የማይሞተው ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ። የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡"
/ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/
@yeabewu
@yeabewu
BY የአባቶች ሃይማኖት
Share with your friend now:
tgoop.com/yeabewu/19