tgoop.com/yeabewu/30
Last Update:
የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ⚪️
November 20, 2024 by ህዳር ፲፪ የ ቅዱስ ሚካኤልን ክብረ በዓል ለምን እናከብራለን?
ሰላም ለዝክረ ስምከ ምስለ ስመ ልዑል ዘተሳተፈ፤ ወልደ ያሬድ ሄኖክ በከመ ጸሐፈ፤ ሶበ እጼውዕ ስመከ ከሢትየ አፈ፤ ረዳኤ ምንዱባን ሚካኤል በከመ ታለምድ ዘልፈ፤ ለረዲኦትየ ነዓ ሰፊሐከ ክንፈ።
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን ለሰው ወገን የሚያዝንና የሚራራ በእግዚአብሔር ጌትነት ዙፋን ፊት ሁል ጊዜ በመቆም ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ በሰማያትም ለሚኖሩ ኃይሎች ሁሉ አለቃቸው ለሆነ ለቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው::
ይህም በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በታላቅ ክብር ሁኖ የነዌ ልጅ ኢያሱ ያየው ነው:: ከእኛ ሰዎች ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ አለው::
ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደለትና በእኔ በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል አለው::
የእግዚአብሔር የሠራዊቱም አለቃ ሚካኤል ኢያሱን የቆምክበት ምድር የከበረች ቦታ ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው:: ኢያሱም እዳለው አደረገ::
ስለዚህም ስለ ልዕልናውና ስለ አማላጅነቱ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ለመታሰቢያው በዓል ተሠራለት::
እርሱ ስለ እኛ የምድሩን ፍሬ ይባርክልን ዘንድ ዝናሙን በጊዜው እንዲያወርድልን የወንዙንም ውኃ እንዲመላልን ነፋሱንም የምሕረት ነፋስ እንዲያደርግልን ሁሉንም የተስተካከለ እንዲአደርግልን ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ይማልድልናል::
እንዲህም ሆነ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ:: የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው:: እነርሱም ሁል ጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር::
ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ:: ለዚህም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለበዓሉ መታሰቢያ ያደርጉ ዘንድ የእርሱን ልብስና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሔደ::
ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ በረከትን ሁሉ ቤቱ ተመልቶ አገኘው:: እጅግም አደነቀ የዚህንም የከበረ መልአክ የበዓሉን መታሰቢያ እንዳስለመደ አደረገ:: የተራቡ ድኆችን ሁሉንም ጠርቶ መገባቸውና ወደየቤታቸው አሰናበታቸው::
ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው:: ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሠነጥቅ አዘዘው:: በሠነጠቀው ጊዜ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ተገኘ::
ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስንና ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው:-
ከዚህ ዲናር ወስዳቹ ለባለ በጉ ለባለ ዓሣውና ለባለ ሥንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ የቀረውን ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ:: በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል::
እነርሱም ሲሰሙ ስለዚህ ነገር ደነገጡ:: እርሱም ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ መሥዋዕታችሁና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ::
አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም አላቸው:: ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት ወጣ:: እነርሱም ሰገዱለት ተአምራቱም የማይቈጠር ብዙ ነው::
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ መልአክ ጸሎትና አማላጅነት ይማረን ይባርከን በስሙ መልካምና በጎ ነገር ሠርተን የተሰጠው ቃል ኪዳን ይድረስ ይፈጸምልን ለዘላለሙ አሜን::
✨ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!!!✨
✞ይቆየን✞
@yeabewu
@yeabewu
BY የአባቶች ሃይማኖት
Share with your friend now:
tgoop.com/yeabewu/30