tgoop.com/yeabewu/42
Last Update:
ኢትዮጵያዊው ሊቅ በሰቈቃወ ድንግል መጽሐፋቸው ላይ የአምላክ ማደሪያ የኾነችው ታቦት ወደ ፍልስጥኤም ሀገር ሄዳ ዳጎንን ሰባብራ እንዳጠፋች ኹሉ፣ አማናዊት የጌታ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያምም ጌታን ይዛ ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ኹሉ እየተሰባበሩ መውደቃቸውን ያስረዳል፡፡
ይህን አባ አርከ ሥሉስ የተባሉ ሊቅ ሲያስረዱ እንዲል ብለዋል፤
ታቦተ አምላክ እስራኤል ጽዮን ዘነገደት ምድረ ኢሎፍሊ
ወቀጥቀጠቶ ለዳጎን ነፍሳተ ብዙኀን ማኅጎሊ
አመ ነገደት ቍስቋመ በኀይለ ወልዳ ከሃሊ
ወድቁ አማልክተ ግብጽ መናብርተ ሰይጣን ሐባሊ
ወተንፍሩ ኵሎሙ ዘቦሙ አስጋሊ
‹‹ወደ ኢሎፍሊ ምድር ተማርካ የኼደች የእስራኤል አምላክ የቃል ኪዳኑ ታቦት ታቦተ ጽዮንን የብዙዎችን ነፍሳት ያጠፋ ዳጎንን ሰባበረችው በዚች ታቦት የተመሰለች ድንግል ማርያምም ኹሉን ማድረግ ከሚችል ከልጇ ጋር ግብጽ ወደሚባል አገር በኼደች ጊዜ የሐሰተኛ ሰይጣን ዙፋኖች የኾኑ የግብጽ ጣዖታት ፈረሱ ጠንቋይ አስጠንቋይ ያላቸው ኹሉ ዐፈሩ።›› በማለት አነጻጽራል። ይኸም ለጊዜው ቢደረግም ለኋላው ግን ምሳሌ ነበር፡፡ ላሞቹ የሰማዕታት፤ ልጆች የልጆቻችው፤ ሠረገላ የመስቀል፤ ልጆቻቸውን ከወደ ኋላ እንዳስተሩ፤ ስማዕታትም የልጅ የገንዘብ ፍቅር አያስቀራቸውምና፤ ሠረገላውን ፈልጠው እንደ ሠዋቸው ራሳቸውን በመስቀል ይሠዋሉና በማለት የብሉይ ኪዳን መተርጕማን ያመሰጥሩታል፡፡
የመልክአ ማርያም ደራሲ ታላቁ ንጉሥ ቃላት የተጻፉባቸው ጽላት የተቀመጡባትን የእግዚአብሔርን ታቦት ጊደሮቹ ከልጆቻቸው ይልቅ በማስበለጥና በመውደድ ይዘዋት ወደፊት እንደነጎዱ፤ እርሱም የልዑል ማደሪያ ለኾነችው ለድንግል ማርያም ያለውን ጥልቅ ፍቅር በድርስቱ ሲገልጥ እንዲህ አለ
ማርያም ጽዮን ታቦት ቃለ ጽድቅ መንፈቀ ዕሥራ
ዕጐላት እምዕጕሊሆን ከመ ኪያኪ አፍቀራ
አፍቀርኩኪ አፍቅርኒ እምይእዜ ለግሙራ
‹‹የሃያ እኩሌታ የሚኾን የእውነት ቃል ማደሪያ ጽዮን ማርያም ሆይ፤ ጊደሮች ከጥጆቻቸው ይልቅ አንቺን እንደእፈቀሩ፤ እኔም ወድጄሻለሁና ከዛሬ ጀምሮ ፈጽሞ ውደጅኝ›› በማለት ገልጦታል፡፡
የሃያ እኩሌታ የሚኾን የእውነት ቃል ሲል ዐሥሩን ቃላት መናገሩ ነው፡፡ ያቺ ታቦተ ጸዮን የማይታይ ረቂቅ ቃል በጽሑፍ እንደገዘፈባት በአማናዊት ጽዮን በእመቤታችን ረቂቅ መለኮት አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ገዝፎባታልና፣ ያቺ የዐሥሩ ቃላት ማደሪያ እንደሆነች እመቤታችንም የዐሥሩ ቃላት ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ ናትና፣ በዚያች አምልኮት እንደጸና በእመቤታችንም አምልኮተ እግዚአብሔር ጸንቷልና፣ ያቺ አራት ማዕዘን እንደሆነች እመቤታችንም ቃል ኪዳንዋ በአራቱ ማዕዘን ይደርሳልና፤ አንድም በአራቱ ማዕዘን ያሉ ክርስቲያኖች ሰአሊ ለነ ቅድስት እያሉ ይማፀኗታልና፡፡ ያቺ መማሪያ ፊደል የረቂቅ ቃል መገለጫ እንደሆች እመቤታችንም የአካላዊ ቃል መገለጫ የኀጥኣን መማሪያ ፊደል ናትና።
አባ ጊዮርጊስ ‹‹ትመስሊ ፊደለ ወትወልዲ ወንጌለ ወታገምሪ መስቀለ፡፡›› ፊደልን ትመስያለሽ፤ ወንገልን ተወልጃለሽ መስቀልን ትወስኛለሽ ሲል ይነግረናል፡፡
ዳግመኛም ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በምሥጢር ሲራቀቅ ‹‹አንቲ ውእቱ ጽዮን ታቦተ አምላከ እስራኤል እንተ ነገደት ምድረ ኢሎፍሊ ወበህየ አውደቀቶ ለዳጎን፡፡›› ወደ አሎፍሊ ምድር የሄደች የእስራኤል አምላክ ማደሪያ ጽዮን አንቺ ነሽ፤ በዚያም ዳጎንን የጣለችው ጣዖት አምላኪዎቹንም የቀሠፈቻቸው በአመጣጧም ከአዛጦን ሰዎች ካሳን የተቀበለች: ከካሳዋም ጋር እንቦሳ ባላቸው ላሞች አስጭነው የሸኟት ከርሷም ጋር የወርቅ ሳጥኖችን በጐኗም የበድን ሣጥን ሥርዐትን አልሠሩም፣ ነገር ግን በእርሷ ዘንድ ካለ ከወርቅ መሣሪያና ከሣጥን ጋራ ላኳት፤ በእንግድነቷ ወቅትም በአሳደራት ጊዜ ወደ ቤቱ በመግባቷ እግዚአብሔር የአብዱራን ቤት ባረከ በማለት የምሳሌዋን እሙንነት በሰፊው ገልጧል፡
ይኽቺም የእግዚአብሔር ታቦት በቤተ ዐሚናዳብ ኻያ ዓመት ተቀምጣለች፤ ከዚያም የሳኦል ዘመን አልፎ የእግዚአብሔር ወዳጅ ዳዊት በነገሠ ጊዜ በአዲስ ሠረገላ አድርገው ከቤተ ዐሚናዳብ አውጥተው በበገና፣ በመሰንቆ፤ በከበሮ፤ በነጋሪት በጸናጽል እግዚአብሔርን እያመሰገነ ይዘዋት ሲመጡ የእግዚአብሔርን ታቦት ዖዛ በድፍረት በመያዙ እግዚአብሔር ቀሥፎት ወዲያውኑ በታቦቷ አጠገብ ሕይወቱ አልፏል፤ ያን ጊዜ ነቢዩ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት ያደረገችውን ተአምራት ተመልክቶ፤ እግዚአብሔር በእርሷ እንዳደረ በማመን የፍርሃት ተውጦ የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል?› በማለት ለታቦቷ ያለው ክብር ገልጧል፡፡ ፪ኛ ሳሙ ፮ ፥ ፱
በዘመነ ሐዲስም በተመሳሳይ መልኩ ጌታን በማኅፀኗ የተሸከመች የልዑል እግዚአብሔር ማደሪያ አማናዊት ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በኼደች ጊዜ ኤልሳቤጥ ልክ እንደ ዳዊት መንፈስ ቅዱስ መልቶባት፤ የጌታ ታቦት (ማደሪያው) መሆኗን ተረድታ፤ ድምፅዋን አሰምታ ‹‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል?›› በማለት ለቅድስት ድንግል ማርያም ያላትን ታላቅ አክብሮት እንደ ዳዊት ገልጣለች። ሉቃ ፩ ፥ ፵፫ ከዚያም ዳዊት ይኽነን ታላቅ ቃል ከተናገረ በኋላ የእግዚአብሔር ታቦት በአቢዳራ ቤት ለሦስት ወር ያኽል እንደተቀመጠች ፪ኛ ሳሙ ፮ ፥ ፲፩ በተመሳሳይ መልኩ የአምላክ ማደሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በካህኑ በዘካርያስ ቤት ለሦስት ወር ተቀምጣለች። ሉቃ ፩ ፥ ፶፮ ዖዛ ተቀሥፎ ከሞተ በኋላ የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አቢዳራ ቤት ገብታ ቤቱ ለሦስት ወር በበረከት እንደተመላ ኹሉ፤ በተመሳሳይ መልኩ ዘካርያስም የመልአኩን ቃል ባለመቀበሉ ከተረገመ በኋላ እውነተኛዪቱ የአምላክ ታቦት ድንግል ማርያም በቤቱ ለሦስት ወር ያህል ተቀምጣ ቤቱን ባርካለታለች፡፡ ሉቃ ፩ ፥ ፳
እግዚአብሔር በታቦቷ ምክንያት የአቢዳራን ቤት እንደባረከ ኹሉ የዘካርያስንም ቤት በእመቤታችን ምክንያት የባረከው መኾኑን ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሲገልጥ ‹‹ድንግል በምሥጢር የተመላ ታቦትን ኾና ትኖራለች፣ የካህናት ወገኖችም ደስ ይላቸዋል፣ ያከብሯታልም›› በማለት ታቦትነቷን አጕልቶ አስተምሯል፡፡
በተጨማሪም የእግዚአብሔር ታቦት ከቤተ አቢዳራ ወደ ዳዊት ከተማ ስትገባ፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ከደስታው ብዛት የተነሣ የጌታ የክብሩ መገለጫ በኾነችው በታቦቷ ፊት እየዘለለ እንዳመሰገነ ኹሉ ፪ኛ ሳሙ ፮ ፥ ፲፪ አካላዊ ቃልን በማኅፀኗ የተሸከመች የአምላክ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያምም ወደ ተራራማው ሀገር ወደ ይሁዳ ከተማ ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በኼደች ጊዜ፤ ታላቁ ነቢይ መጥምቁ ዮሐንስ በእናቱ ማኅፀን ኾኖ ከደስታው ብዛት የተነሣ እየዘለለ አመስግኗል። ሉቃ ፩ይኽነን ምሥጢር ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሲያብራራ ‹‹ንጉሡ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይዘል ነበር፤ ከልቡ ደስታ የተነሣ ለንጉሣውያኑ ደንብ አልታዘዘም፤ እንዲኹ ዮሐንስ ደግሞ ገና ፅንስ ሣለ ከደስታው የተነሣ ከዳዊትም በላቀ ኹኔታ ዘለለ፣ ፅንስ ቢኾንም የእርሱ ባልኾነው በዚኽ ዕድሜ አልተገታም፣ ድንግል እና ቡርክት የኾነችው እናት የእግዚአብሔር ቤት ምስጢራት ከመሉባት ታቦትም በላይ ውብ ነበረች፤ ዳዊትም በአክብሮት በታቦቱ ፊት ዘለለ፤ ይኽም ዮሐንስ በማርያም ፊት ሊዘል እንዳለ አስቀድሞ ያሳይ ነበርና፤ ከዳዊት በቀር ንጉሥ መዝለሉ ተሰምቶ አይታወቅም፤ ሕፃን መዝለሉም እንዲኹ ነቢያት ካህናት የእግዚአብሔርን ልጅ መንገድ አስቀድመው አመለከቱ፤ እርሱም በመጣ ጊዜ ይሹት የነበሩትን ምልክቶች ፈጸማቸው፤ የጌታውን የንጉሡን ምልክት ይጠቁም ዘንድ፤ ዳዊት
BY የአባቶች ሃይማኖት
Share with your friend now:
tgoop.com/yeabewu/42