tgoop.com/yeresulnfkrmeglecha/737
Last Update:
የላይ ገንዳው ዘማች!
አሰላሙዓለይከ ያሷሒበል ኢስራዕ ወል ሚዕራጅ!
የአርሹ ባለቤት መረጣቸው። ሙሐመድ ብሎ ሾማቸው። ወደርሱ ጉዞ ጠራቸው። የላይ ገንዳን ግርዶ ገላለጠላቸው። የልቅናን ሸማ አለበሳቸው። ማንም ያልደረሰበት አደረሳቸው። ሥማቸውን ከሥሙ አድርጎ አሳያቸው። አይገርምህም ወይ የአላህ መለገስ መካ ተወልዶ አርሽ ላይ መንገስ?! በአርሹ ድንኳን ተሞሸሩበት። ጅብሪል የፈራውን የአርሽ የኩርሲይ ባሕር እንዳሻቸው ዋኙበት። የሲድረል ሙንተሐውን፣ የረፍረፉን፣ የመቃመል መሕሙዱን ጢሻ እየጣሱ አለፉት። የመዲናው አንዋር የሰማዩን ቀበሌ አበራው። ሰባ ሺውን ግርዶ በእጁ ገለጠው። ከኋላ መጥቶ ሁሉን በለጠው። ለተኳለ ለተዘዬነው ሙሽራ መለክ አሸርጦ አገልድሞ አደገደገ። ሚዜ ሊሆን ተሰበሰበ። በአርሽ የአዘል ሽቶ ተርከፈከፈ። ብኹር ተነሰነሰ። የቁድራ ጢስ ተጓፈጠ። የኑር ቄጤማ ተጎዘጎዘ። የነቢ ደስታ ታወጀ። ለዛም ነው ብዙ ሙሒቦች በዚህ ሌሊት መውሊድ የሚያወጡት። ኑሕ ቢወደድ፣ አደም ቢነሳ፣ ኢብራሒም ኸሊል ቢባል፣ ኢሳ ቢወሳ ያለ ነቢ በአርሽ የሰገደ አንድም የለም። አዎን ጌትዬ ለነቢ የሰጠውን ለማንም አልሰጠም። ለ‘ርሳቸው ያሳዬውንም ለማንም አልገለጠም። ከስጦታዎቹም ሁሉ በላጩ ሲዲቁ ሰይድ አቡበክር ረ.ዓ ሲቀሩ ሰዎች አይደለም በእውን በህልም እንኳን መከሰቱን ለማመን የተቸገሩበት፣ የመካ ጣኦታውያን የተሳለቁበት፣ በተከበረው ረጀብ ከመካ እስከ አቅሷ ከዚያም ወደ ሰማዬ ሰማያት ቡራቅ ጋልበው ያደረጉትና ተኝተው የነበረበት ፍራሽ ሞቅታው እንኳን ሳይበርድ የተመለሱበት ከስሌት በላይ የሆነው የኢስራዕና የሚዕራጅ ጉዞ ነው። ዓመል ሁዝን ነበር የሀዘን አመት። ነብዬ ሁለቱን ታላላቅ ምርኩዞቻቸውን እናታችንን ኸዲጃን ረ.ዓ እና አጎታቸውን አቡ ጧሊብን ያጡበት። ግና ሳይደግስ የማይጣላው ጌታ ሃዘናቸውን መርሻ፣ ላጡት መካሻ፣ ውድቀት እንዳይሰማቸው የበለጠ ከፍ ማድረጊያ ሰጣቸው።
የሆነው እንዲህ ነበር።
ከወደ ሒጃዝ ምድር፣ በመካ ዙሪያ አንድ ክቡር ሰው ጋደም ብለዋል። የፈጅር ወገግታ ከመቅደዱ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ የዚህ ሰው በር ተንኳኳ። የመላዕክቱ ሁሉ አለቃ ሰይድ ጂብሪል በር ላይ ቆሟል። "ዛሬ የአላህ እንግዳ ነህና ተከተለኝ" አለ። ነቃ አሉና ውዱን ልብሳቸውን ተላብሰው ወደ መስጂደል ሐረም ሜዳ ወጡ። እኚህ ክቡር የአላህ ነብይ ይህንን ወዳጃቸውን ተከትለውት ወደ ውጪ ሲወጡ ሰይድ ሚካኢል የጀነቱን በቅሎ ቡራቅን በልጓሙ ይዞ ተመለከቱት። ተደነቁ። ወደ እርሱ ቀረቡ። ቡራቅ ነብዬን ያዬ ጊዜ በብዙ ሐያእ አድርጎ ተንበረከከ። ሱጁድም ኢክራም አደረገ። ጊዜ አላባከነም ሰይዱና ጂብሪል ተሳፈረው፣ ከዚያም ሰይዳችን ሙሐመድ (ሶለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ተፈናጠጡ፣ ሰይዱና ሚካኢል ተከተለና ጉዞ ጀመሩ። ወደተቀደሰችው ምድር፣ ወደተከበረው መስጂድ፣ ወደ መስጂደል አቅሷ አቀኑ። እዚያ ሰፊ ሜዳ ላይ መለክ የተባለ ሁሉ፣ ነብይ እና አርሳል በሙሉ፣ የጀነት ሁር በጠቅላላው ሰልፍ አሳምረው ቆመዋል። አውሊያው ሳዳቱ በሩሕ ሐድሯል። ከፊሉ በጀሰድም ተጥዷል ብለው በሰነድ ነግረውናል ሸይኾቻችን። እዚያ ሲደርሱ እኚያን በሩሕ የቀደሙ ነብይ ከሁሉም ኸልቅ ጋር አስተዋወቃቸው። ከአባታቸው አደም ጋር አዘያይሮ፣ ከወንድማቸው ኢስማዒል ጋር አስተቃቀፋቸው፣ ከመሪያቸው ከነቢ ኢብራሒም ጋር አቀማመጣቸው። ይህ ሁሉ በቅፅበት ተከወነ። ከዚያም አንቢያእ በሞላ በየደረጃው ተሰለፈ። መላኢካው እነርሱን ከበበ። ሰይዱና ጂብሪል የድንገቴ "ያ ሙሐመድ" ሲል ተጣራ። ሰይዱል ዉጁድም "ለበይክ" አሉ። "ወደዚህ ምኩራብ ቅረብ፣ ተቀደም፣ አሰግድ" አላቸው። ለሶላተል ኢብራሂምያ ጥሪ ተደረገ። በዚያ ዘመን ገና የነብያችን ሶላት አልተደነገገምና ሁለት ረከዓ ተሰገደ።
ነብያቱ ከሶላቱ መጠናቀቅ በኋላ ወደየመቃማታቸው ተመለሱ። ወዲያውኑ ጉዞ ቀጠለ። ወደ ሰማይ። የአንደኛው ሰማይ ተንኳኳ። በሰይዳችን ስም ተከፍቶ ዘለቁ። በየሰማዩ ነብያትን ዳግም አገኙ። ሰይዱና ኢብራሂም በይተል መእሙርን ደገፍ ብለው ሲያገኟቸው "ለሕዝቦችህ ሰላምታዬን አድርስልኝ" አሏቸው። እኛም "ወዓለይከ ሰላም ያኸሊለላህ" ብለናል። የሰማዩ ጉብኝት አልቆ ከከውኑ ክልል አለፉ። የፍጥረት መባቂያ ደረሱ። እዚያ ላይ ሰይዱና ጂብሪል ነብያችንን ከኑሩ ባህር ገፍተር አድርገው "በል ሂድ እኔ ቦታዬ እዚህ ነው" አሉ። ነብዬ ተደናገራቸው። የሰማዩን መንገድ አዋቂው፣ ጋባዡ እና አስጎብኚው በቃኝ ማለቱ አስፈራቸው። ከዛማ አንድም ፍጥረት ያልደፈረውን ሰይዳችን ደፈሩት። አለፉት። ተሻገሩት። የኑር ስብስቡ በሌላ ኑር ተዘፈቁ። ከመብረቅ ቅፅበት በፈጠነ፣ ጊዜ እና ቦታ፣ ቁጥር እና ስፍራ፣ አቅጣጫ እና እንዴታ በሌለው ዓለም ተሰየሙ። ራሳቸውን የዓርሽ ምንጣፍ ላይ አገኙት። አቆራርጠው ያለፉት ያ ሁላ ግርዶ ድንገት ትውስ ቢላቸው ተደናገጡ። "ፊ ሐድረቲ ሹሁዲ ረህማን" ተሰይመው መሆኑን ሲያውቁ ድፍት አሉ። ዒባዳ ለጠቁ። ጌታቸውን በማወደስ ዋለሉ። "አትህያቱ" እያሉ ተደገደጉ። የጌታቸውንም ሰላምታ ተሸለሙ። የወዳጆቹ ወግ ደራ። ደጉ ሰው በደስታውም በሃዘኑም እኛን ካላነሳሱ አይሆንላቸውም። "አሰላሙዓለይከ አዩሃ ነቢዩ!" የተባሉ ጊዜ ዓለሙን በሚያስረሳ የደስታ ማማ ላይ ሆነው አልረሱንም። "አሰላሙዓለይና ወዓላ ኢባዲላሂ ሷሊሒን!" ብለው በዛ ሐድራ ወሊዮቹ ጋር ጣዱን። በዚያ እነ ሰይድ ጂብሪል ሁሉን በሚረሱበት ዓለም ኡመታቸውን አስታወሱ። ሁሉን ዋ ለነፍሴ ዋ ለራሴ በሚያስብለው የጭንቅ ጊዜም ኡመቲ ኡመቲ ነው የሚሉት።
ኢስራዕ ተአምር ነው። ጌትዬው ተዓምርነቱን ሲገልፅ "ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ያስኬደው ጌታ ጥራት ይገባው!" ይልና "ከተዓምራቶቻችን ልናሳዬው!" ይላል። ጉዞውን እንዳጠናቀቁ አቡ ጀሕል ስለ ተዓምሩ ሰማና ሰዎች ሰብስቦ አሳቀባቸው። ሌሎቹም አምኖ መቀበል ከበዳቸው። አቅሷን የሚያውቁ ሰዎች ሊፈትኗቸው ስለ አካባቢው ጠይቀዋቸው ማስታወስ ባይችሉም አላህ አቅርቦ አሳይቷቸው አስረድተዋቸው ትክክል መሆናቸውን መስክረዋል። እንደዚሁም ሌላ በጉዟቸው ያጋጠማቸውንና አስረጂ ይሆንልኛል ያሉትን ተናግረው ሰዎቹ ሲያጣሩ ሃቅ ሆኖ አግኝተውታል። ግና ሲደፈንብህ ማስረጃም መረጃም አያስረዳህምና አልተቀበሉም። አስረዳን የምንለው ለዚህ ነው። ኢስነይንና ኢስራዕ ገጠመ። ምን ይሁን ትላለህ ከዚህ የበለጠ! እንባ አበሹ ጌታ፣ ለሀዘናቸው መፅናኛ የላከው ጌታ፣ ከሃም ጘም መውጫ ይላክልን። ሲሩ ባልታወቀው የኻሉቅና መኽሉቁ ግንኙነት ይሁንበት!
ለነቢ ደስታማ ለይሉን እንቆማለን። ቀኑን እንፆማለን። እንኳን አደረሳችሁ!
አሏሁመሶሊ ዓላ ሙሐመዴ የጅብሪል ወዳጅ የአላህ ባለሟል ሰይዲ ጀማሉል ጀማል!💚💚💚 💚💛❤️
💚💛❤️
💚💛❤️
ﷺ❤️ﷺ ﷺ ﷺ ﷺ ﷺ ﷺ
BY ሁስነል ኹሉቅ
Share with your friend now:
tgoop.com/yeresulnfkrmeglecha/737