tgoop.com/z_bishara/799
Last Update:
የመለያው ቀን
እያንዳንዱ ስልጣኔ ከማበቡና የልቅና ማማ ላይ ከመድረሱ በፊት ወሳኝ ታሪካዊ ክስተት ያሳልፋል፡፡ ለሙስሊሞች ይህ ወሳኝ ክስተት ረመዳን 17 2ኛ ዓ.ሂ የተካሄደውና በቁርአን ስሙ የተጠቀሰው ታላቁ የበድር ጦርነት ነው፣ አላህ ይህን ዕለት የውመል ፉርቃን(የመለያው ቀን) ብሎ ጠርቶታል፣ እውነትና ውሸት የተለዩበት የየራሳቸውን ጎራ ይዘው ፊት ለፊት የተያዩበት ዕለት ነው፡፡
‹‹...በዚያም እውነትና ውሸት በተለየበት ቀን፣ ሁለቱ ጭፍሮች በተገናኙበት(በበድር) ቀን…››አል አንፋል 41
የአላህ መልእክተኛ ሰ.ዐ.ወ የቁረይሾችን የንግድ ቅፍለት ለመቆጣጠር ከተወሰኑ ሰሃቦች ጋር ሆነው ከመዲና ወጡ፤ የቅፍለቱ መሪ የነበረው አቡ ሱፍያን ይህ ወሬ ሲደርሰው ወደ መካ መልእክተኛ ላከ፡፡ ቁረይሾችም 1300 የጦር ሰራዊት፣700 ግመሎችና በቁጥር የበዙ ፈረሶችን ይዘው ተንቀሳቀሱ፡፡ የሙእሚኖች ብዛት ከ313-319 ሲሆን 70 ግመል እና 2 ፈረስ ብቻ ነበር የያዙት፡፡ ነቢ ሰ.ዐ.ወ የባልደረቦቻቸውን ሃሳብ መስማት ፈለጉና ውጊያ እናድርግ ወይስ እንመለስ ብለው አማከሯችው፤ ምክንያቱም አወጣጣቸው ቅፍለቱን ለመማረክ እንጂ ለጦርነት አልነበረም፡፡ በመጀመሪያ አቡበክር ተነሱና ጥሩ ንግግር አደረጉ፤ ዑመርም በመቀጠል ተናገሩ፤ ከዚያም ሚቅዳድ ኢብን ዐምር ተነሳና፡-
‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ፡ አላህ ያመላከተዎትን ተግባር ይፈፅሙ እኛ ከጎንዎ ነን፤ በአላህ እምላለሁ እስራኤሎች ለሙሳ ‹አንተና አምላክህ ሂዱና ተዋጉ፤ እኛ አዚህ ተቀምጠን እንጠብቃችኋለን› እንዳሉት እኛ አንልዎትም፡፡ ይልቁንም እርሶና አምላክዎ ሄዳችሁ ተዋጉ፤ እኛም ከናንተ ጋር እንዋጋለን፡፡ በእውነት በላከዎ ጌታ እምላለሁ ወዳሻዎ ቦታ ብትወስዱንም እስከመጨረሻው እንከተሎታለን፡፡›› አለ፤ ነቢ ሰ.ዐ.ወ በንግግሩ ተደስተው ጥሩ ብለሀል አሉትና ዱዓእ አደረጉለት፡፡ ሁሉም ሰሀቦች እንደ ሚቅዳድ ታዛዥ እንደሆኑ ያውቃሉ፤ ነገር ግን አሁንም ደግመው ሀሳባቸውን ጠየቋቸው፤ ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ፡ አስተያየታችሁን ስጡኝ›› አሉ፡፡ አንሳሮችን ማለታቸው ነው፤ ምክንያቱም አንሳሮች ከነቢ ሰ.ዐ.ወ ጋር የዐቀባን ስምምነት በተዋዋሉ ጊዜ መዲና መጥቶ የሚያጠቃቸውን ጠላት እንጂ ከመዲና ውጪ ወጥተው እንዲዋጉ አያስገድዳቸውም፡፡
ሰዐድ ኢብን ሙዓዝ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ፡ የኛን አስተያየት ነው የፈለጉት? ›› ብሎ ጠየቃቸው እሳቸውም አዎ አሉት፡፡ እሱም አንሳሮችን ወክሎ እንዲህ ተናገረ፡-
‹‹ በእርሶ አምነን እውነት ብለን ተቀብለንዎታል፤ ያመጡት መልዕክት እውነት ስለመሆኑም መስክረናል፤ እርስዎን ለመታዘዝ ቃልኪዳን ገብተናል፤ የአላህ መል/እክተኛ ሆይ፡ የሚፈልጉትን ይፈፅሙ በእውነት በላክዎ አምላክ እምላለሁ ይህን ባህር ሰንጥቀን እንድናልፍ ቢያዙን እንኳ እናልፈዋለን፤ ከመካከላችን አንድም ሰው ወደኋላ አይቀርም ነገ ከጠለት ጋር ብንፋለም የምንጠላ አይደለንም በጦርነት ላይ ታጋሾችና ፅኑዎች ነን፤ ከኛ የሚደሰቱበትን ነገር አላህ ያሳይዎ ይሆናል በአላህ በረከት የታየዎትን ይፈፅሙ፡››
ነቢ ሰ.ዐ.ወ በሰዕድ ንግግር ተደሰቱ፤ ወኔያቸውም ይበልጥ ተነሳሳ፤ “ተጓዙ አይዟችሁ አላህ ከሁለት በጎ ነገሮች አንዱን እንደሚገጥመኝ ቃል ገብቶልኛል፤ በአላህ እምላለሁ ሰዎች (ጣኦታውያን) ሲረፈረፉ ይታየኛል” አሉ፡፡
የዛን ቀን ምሽት አላህ ሱ.ወ ዝናብ አወረደ ከሀድያንን ያዳክመች፣ ለሙእሚኖች ጥንካሬ የጨመረች ዝናብ አዘነበ፡፡ “ ከርሱ የሆነን ሰላም ሊለግሳችሁ በእንቅልፍ በሸፈናችሁ ጊዜ፣ እንዲሁም በርሱ ሊያፀዳችሁ፣ የሰይጣንንም ጉትጎታ ሊያስወግድላችሁ፣ ለልቦቻችሁም ጥንካሬን ሊያጎናፅፍና እግሮቻችሁንም (ውጊያ ላይ) ሊያፀና ከሰማይ ውሃን ባወረደ ጊዜ (የሆነውን አስታውሱ) አል አንፏል 11
ጣኦታውያን ሲገለፁና ሁለቱ ሀይሎች ሲተያዩ የአላህ መልዕክተኛ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለው አላህን ለመኑ፡-
“አላህ ሆይ ቁረይሾች ከነ ትዕቢትና ኩራታቸው አንተን ለመቀናቀን እና መልእክትህን ለማስተባበል እነሆ ታድመዋል፤ አላህ ሆይ ቃል የገባህልኝን ድል ስጠኝ፤ አላህ ሆይ ሽንፈትን አከናንባቸው›› የሰራዊታቸውን ረድፍ አስተካክለው ከጨረሱ በኋላም አምላካቸውን አጥብቀው ከመማፀን አልተቆጠቡም፤ “አላህ ሆይ ቃልህን እንድትሞላ እማፀንሀለው›› እያሉ ይለምኑት ነበር፤ ጋቢያቸው ከትከሻቸው እስኪወድቅ ድረስ ዱአቸው በረታ፤ አላህም ለመላእክቱ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላለፈ፡-
“እኔ ከናንተ ጋር ነኝ እማኞችን አጠናክሩ፤ በነዚያ በካዱት ሰዎች ልቦች ውስጥ ፍርሀትን እለቃለሁ….›› አልአንፋል 12 ለመልዕክተኛውም እንዲህ ሲል አበሰራቸው፡
“ተከታትለው በሚወርዱ ሺህ መላዕክት እገዛ አልክላችኋለሁ”
“አዎን ብትታገሱና ብትጠነቀቁ ከዚህም ፍጥነታቸው (ጠላቶቻችሁ) ቢመጡባችሁ፡ ጌታችሁ ምልክት ባላቸው አምስት ሺህ መላእክት ይረዳችኋል›› አሊ ዒምራን 125፡፡ መላእክት በወረዱ ጊዜ ነቢ ሰ.ዐ.ወ ይህንን የቁርአን አንቀፅ አነበቡ
“ስብስበቸው ድል ይምመታል፡ ጀርባዎቻቸውንም ይዞራሉ” አልቀመር 45፡፡
በእጃቸው እፍኝ አፈር ቆነጠሩና ወደ ቁረይሾች አቅጣጫ በመዞር “ፊቶቻችሁ ይበላሹ” እያሉ በተኑት፤ አሸዋው በእያንዳንዱ ጣኦታዊ አይንና አፍንጫ ውስጥ ገባ፡፡
ጦርነቱ በጣኦታውያን ከባድ ሽንፈት፡ በሙስሊሞች አንፀባራቂ ድል ተደመደመ፡፡ ከሙስሞች 14 ሰማዕታት ሲኖር ከጣኦታውያን 70 ሰዎች ተገድ' ለው 70ዎቹ ተማረኩ፤ ከሙታንም ሆነ ከምርኮኞች አብዛኛዎቹ መሪዎችና በላባቶች ነበሩ፡፡
BY የቢሻራው በር✍
❌Photos not found?❌Click here to update cache.
Share with your friend now:
tgoop.com/z_bishara/799